የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ላለፉት አራት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የስድስተኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች የሁለተኛው ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 ዳንኤል ተሾመ አሁንም ማስገረሙን ቀጥሏል

የአዲስ አበባው የግብ ዘብ ዳንኤል ተሾመ ከቡድኑ አስደናቂ ሰሞነኛ ማንሰራራት በስተጀርባ አሁንም ቁልፉ ሰው መሆኑን እያስመሰከረ ይገኛል።

በተጫዋቾች አለመኖር ምክንያት ቡድኑን በአምበልነት እየመራ የሚገኘው ግብ ጠባቂው ሀዲያ ሆሳዕናን በጠባብ ውጤት ባሸነፉበት ጨዋታ የፍፁም ቅጣት ምትን ከማዳን ባለፈ በጨዋታው እጅግ አደገኛ የነበሩ ሙከራዎችን በማምከን ለቡድኑ አለኝታ መሆኑን ዳግም አስመስክሯል።

በአምናው የውድድር ዘመን በአዳማ ከተማ ቆይታ ያደረገው ግብጠባቂው በተለይ በመጀመሪያው ዙር በአንዳንድ ጨዋታዎች እጅግ አስደናቂ የነበሩ የጨዋታ ቀናትን ቢያሳልፍም በወጥነት ይህን አቋሙን ማስቀጠል ተስኖት በተቃራኒው መጥፎ የጨዋታ ዕለትን ሲያሳልፍ በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ዘንድሮ ግን በአዲስ አበባ ከተማ በአንፃራዊነት በወጥ ብቃት ቡድኑን እያገለገ ይገኛል።

👉 የዑመድ ኡኩሪ የመጀመሪያ ግብ ፍለጋ

ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተቀዳሚ ተመራጭ የነበረው ዑመድ ኡኩሪ አሁንም የመጀመሪያ የሊግ ግቡን እያሰሰ ይገኛል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ከዓመታት የግብፅ ሊግ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚመለስውን ዝውውር ፈፅሞ ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቅሎ በአምናውም ሆነ በዘንድሮው የሊግ ውድድር በአመዛኙ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ ዕድል ቢያገኝም እስካሁን ድረስ ከግብ ጋር መገናኘት እንደተሳነው ቀጥሏል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በአዲስ አበባ ከተማ ሲረታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሀዲያ ሆሳዕናዎች ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ዑመድ የመምታት ኃላፊነት ቢሰጠውም ኳሷን መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

ከግብ ጋር የተራራቀው ዑመድ የራስ መተማመኑ በጣም ከፍተኛ በሚባል ደረጃ መውረዱን በሚያሳብቅ ሁኔታ ውሳኔዎቹ እርግጥነት የጎደላቸው ብሎም ከግብ መራቁን መነሻ ባደረገ የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ በመውደቁ ከአዕምሮ መዛል (Frustration) ጋር በተያያዘ ሜዳ ላይ ተደጋጋሚ ንትርኮች ውስጥ ተሳታፊ ሲሆን እየተመለከተን እንገኛለን። እስካሁን በሊጉ ሁለት ግቦችን ብቻ ላስቆጠረው የሀዲያ ሆሳዕና የአጥቂ መስመር ግቦችን እያስቆጠረ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ የቡድኑ ቁልፍ ሰው የሆነው ዑመድ ወደ አግቢነቱ መመለስን አጥብቆ የሚሻ ይመስላል።

👉 ለቡናማዎቹ ውለታን የዋለው በረከት አማረ

ኢትዮጵያ ቡና መከላከያን 1-0 በረታበት ጨዋታ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ሜዳ ተቀይሮ የገባው በረከት አማረ ፍፁም ቅጣት በማዳን ለቡድኑ ውለታ መዋል ችሏል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች የአንድ ግብ ልዩነቷን ለማጣፋት እየታተሩ የነበሩት መከላከያዎች በ88ኛው ደቂቃ ኤርሚያስ ኃይሉ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ በሰራው ጥፋት መነሻነት መከላከያዎች የፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኙ በተቃራኒው የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል።

አቤል ማሞን ተክቶ የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ የጨዋታ ተሳትፎን ማድረግ የቻለው በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከጅማ አባ ጅፋር ዳግም ወደ ቀድሞ ቤቱ ኢትዮጵያ ቡና የተለመሰው በረከት አማረ የመጀመሪያ ተሳትፎውን ከቢኒያም በላይ የተመታበትን የፍፁም ቅጣት ምት በማዳን አድርጓል።

በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዘመን አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በቋሚዎቹ መካከል በረከት አማረን እና አቤል ማሞን በማፈራረቅ ሲጠቀም የነበረ ሲሆን በአምናው እና በዘንድሮው የውድድር ዘመን ግን ተመሳሳይ ግብ ጠባቂዎችን በወጥነት እየተጠቀመ ይገኛል። በዚህም መነሻነት በረከት አማረ በተጠባባቂነት ለመቀመጥ እየተገደደ ይገኛል።

ታድያ ፍፁም ቅጣት ምት በማዳን ለቡድኑ ውለታ የዋለው በረከት በቀጣይ ጨዋታ የሚያሳየው እንቅስቃሴ ለቋሚነት በሚኖረው ፉክክር ውስጥ ዳግም ምርጫ ውስጥ እንዲገባ አሰልጣኙን ለማስገደደ ወሳኝ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

👉 ተስፋ ሰጪው አላዛር ማርቆስ

ወጣቱ ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ጅማ አባ ጅፋር በባህር ዳር ከተማ 2-0 በተሸነፈበት ጨዋታ የጨዋታው ውጤት በዚህ ልዩነት ስለመጠናቀቁ በጅማ አባ ጅፋሮች በኩል የሚመሰገነው ተጫዋቾች ነበር።

ደካማ የውድድር ዘመን እያደረጉ የሚገኙት ጅማ አባ ጅፋሮች በቅርቡ በውሰት ውል ካስፈረሟቸው አራት ወጣት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አላዛር ማርቆስ ቡድኑን ከተቀላቀለ ወዲህ ከተደረጉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለቱን በቋሚነት ጀምሯል።

በሀዋሳ ከተማ የክለብ እግርኳስን ጅማሮ ያደረገው እና 2010 በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና እየተመራ በታንዛኒያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የሴካፋ 17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ቡድን አባል የነበረው አላዛር በውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ መመረጡ አይዘነጋም።

በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታን ባደረገበት የድሬዳዋ ከተማው ጨዋታ ሦስት ግቦችን ቢያስተናግድም ጥሩ እንቅስቃሴን ማድረግ የቻለው ሲሆን በተመሳሳይ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በባህር ዳር ከተማ ቢሸነፉም ወጣቱ ግብ ጠባቂ የግብ ልዩነቱ እንዳይሰፋ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን ሲያድን ተመልክተናል።

በተጨማሪም ወጣቱ ግብ ጠባቂ በተወሰነ መልኩ ከግባቸው ርቀው ለመከላከል ይሞክሩ ከነበሩት የቡድኑ ተከላካዮች በስተጀርባ የባህር ዳር ተጫዋቾች ይጥሏቸው የነበሩትን ኳስ በፍጥነት በመገንዘብ ያቋርጥ የነበረበት መንገድ የተለየ ነበር።

👉 “ዓሊንዶቨስኪ ሱሌይማን”

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ባሳለፍነው ክረምት በተካሄደው የሴካፋ ውድድር ላይ የውድድር ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን ያጠናቀቀው ኤርትራዊው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ለአዲሱ ክለቡ የመጀመሪያዎቹን ግቦች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ማስቆጠር ችሏል።

በባህር ዳር ከተማ በተደረገው የሴካፋ ውድድር ድንቅ ጊዜን ማሳለፍ የቻለው ዓሊ ሱሌይማን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወደ ባህርዳር ካቀና በኋላ በውድድር ዘመኑ መጀመርያ በተደረገው የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ከፋሲል ከነማው ሰዒድ ሀሰን ጋር ከኳስ ጋር በነበረ ፍትጊያ መነሻነት ባጋጠመው የትከሻ ጉዳት ለሁለት ወር ለቀረበ ጊዜ ከሜዳ ርቆ መቆየቱ አይዘነጋም።

ከጉዳት መልስ የቀደመ ብቃቱን መልሶ ለማግኘት እየታተረ የሚገኘው ተጫዋቹ ባህር ዳር ከተማ ጅማ አባ ጅፋርን 2-0 በሆነ ውጤት ሲረታ ሁለት የተጫዋቹን የግል ብቃት የሚያሳዩ ግሩም ግቦችን በማስቆጠር በተከታታይ ጨዋታዎች ከድል ርቆ የነበረውን ቡድኑን መሉ ሦስት ነጥብ አስጨብጧል።

ግቦቹን ካስቆጠረ በኋላም ደስታውን የገለፀበት መንገድ ልክ ፖላንዳዊው የባየር ሙኒክ አጥቂ ሮበርት ሎዋንቨስኪ ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ ደስታውን በሚገልፅበት መንገድ መሆኑ አስገራሚ አጋጣሚ ነበር።

👉 ኦሮ-አጎሮ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል

በክረምቱ ጌታነህ ከበደ እና ሳልሀዲን ሰዒድን የመሰሉ በሀገሪቱ ደረጃ የጥራት ደረጃቸው የላቁ የፊት አጥቂዎችን የለቀቁት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በምትኩ በአሁኑ ስብስባቸው ውስጥ ብቸኛው የፊት አጥቂ የሆነው ኦሮ-አጎሮ ጋር የውድድር ዘመኑን በምን መልኩ ይገፉታል የሚለው ጉዳይ የሚጠበቅ ነበር።

እስማኤል ከሊጉ መጀመር በፊት ቡድኑ በተካፈለበት የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ አመርቂ እንቅስቃሴን ማድረግ አለመቻሉን ተከትሎ ቡድን ሊቸገር እንደሚችል እና ካሉት ፈጣን የመስመር አጥቂ/አማካዮች/ አንዱን በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር መጠቀም ይገባቸዋል የሚሉ ሀሳቦች መንሸራሸር ጀምረው ነበር።

በተመሳሳይ በሊጉ ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ የሊጉን ግቡን ለቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ባስቆጠረበት መንገድ ከፍተኛ ተቃውሞን አስተናግዶ የነበረው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ከዚያ ሂደት መልሰ ባሉት ጨዋታዎች ግን ቀስ በቀስ መሻሻሎችን እያሳየ እንደሚገኝ እያስዋልን እንገኛለን።

ጥሩ የሳጥን ውስጥ አጥቂ መሆኑን እያስመሰከረ የሚገኘው ኦሮ-አጎሮ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በሳጥን ውስጥ ያለውን አቅም በደንብ ያሳየባቸውን ሁለት ግቦች ማስቆጠር ችሏል። በመጀመሪያው ግቡ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ የተቆጣጠረበት እና የሰውነት አቋቋሙ ተከላካዩን ቦታ አስቶ ግቧን አክርሮ በመመምታት ያስቆጠረ ሲሆን ሁለተኛውን ግብ እንዲሁ ተስፋ ባለመቆረጥ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ከሀዋሳ ተከላካዮች ጋር ታግሎ በመንሸራተት አስቆጥሯል።

ከግቦቹ ውጪ ከሳጥን ውጭ አፈትልኮ በመግባት አክርሮ በመምታት ሁለት አስደናቂ ሙከራዎችን ቢያደርግም የሀዋሳው የግብ ዘብ በግሩም ሁኔታ አዳነበት እንጂ ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

በአሁኑ ሰዓት በአምስት ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን የቻለው እስማኤል ኦሮ-አጎሮ ቡድኑ በቀጣይ ጨዋታዎች አጨዋወቱ በወሰነ መልኩ ቀጥተኝነት ላይ ያተኮረ የሚሆን ከሆነ ከተጫዋቹ ብዙ ሊጠቀም እንደሚችል ይገመታል።

👉 ተከላካዮች በፍፁም ቅጣት ምት መቺነት

በሊጋችን ተሳታፊ የሆኑ ቡድኖች የሚያገኟቸውን የፍፁም ቅጣት ምቶች አሁን አሁን የቡድኖቹ የመሀል ተከላካዮች በስፋት ሲመቱ እየተመለከትን እንገኛለን።

በዚህ ረገድ ባለፉት ጥቂት ዓመታት አስቻለው ታመነ ፈር ቀዳጅ ነበር። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተዳሚ የፍፁም ቅጣት ምት መቺ የነበረው ተጫዋቹ የማስቆጠር ንፃሬው ከፍተኛ የሚባል ነው።

በተመሳሳይ የአሁኑ የቡድን አጋሩ ያሬድ ባየህ በተመሳሳይ የፋሲል ከነማ ተቀዳሚ መቺ ሲሆን አሁን አሁን ደግሞ የአርባምንጩ አምበል ወርቅይታደስ አበበ ፣ የሰበታው በረከት ሳሙኤል እንዲሁም የሀዋሳ ከተማው ዓዲስአለም ተስፋዬ የፍፁም ቅጣት ምት ኃላፊነት ወስደው ሲመቱ እየተመለከትን እንገኛለን።

ምናልባት ከላይ የጠቀስናቸው ተጫዋቾች የካበተ ልምድ ያላቸው እንደመሆናቸው ከፍፁም ቅጣት ምት ጋር ተያይዞ ያለውን ጫና ተቋቁመው እንዲያስቆጥሩ በማሰብ የተመረጡ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

👉 የፍሬው ሰለሞን ግልፍተኝነት

በኢትዮጵያ እግርኳስ ባለፉት አስር ዓመታት ከተመለከትናቸው ጥሩ የአጥቂ አማካዮች መካከል አንዱ የሆነው ፍሬው ሰለሞን በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጅማሮ ጥሩ ጊዜያትን እያሳለፈ እንደመገኘቱ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የመጨረሻው የብሔራዊ ቡድን ስብስብ አባል መሆን ችሏል።

ከሜዳ ላይ ካለው እንቅስቃሴ ባለፈ ግን ተጫዋቾቹ በአንዳንድ አጋጣሚዎች “ምን ነካው?” የሚያሳኙ ከስሜታዊነት የመነጩ ያልተገቡ ድርጊቶችን ሜዳ ውስጥ ሲያሳይ እየተመለከትን እንገኛለን።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም ከአዳማ ከተማ ጋር በነበራቸው ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ በአንድ አጋጣሚ ከአቡበከር ወንድሙ ጋር ኳስ የጋራ ኳስን ተከትለው አቡበከር ሸፍኗት ኳሷ ወደ ውጭ እንድትወጣ ካደረገ በኋላ ፍሬው ሰለሞን ወደ መጫወቻ ሜዳ ሲመለሱ ድንገት ሳይጠበቅ ተንደርድሮ አቡበከር ወንድሙን ያነቀበት ቅፅበት ብዙዎችን ያስደነገጠ ነበር።

ከፍሬው እንቅስቃሴ መረዳት እንደሚቻለው አቡበከር በክርኑ ሊመታኝ ሙከራ አድርጓል የሚል ተቃውሞ እንዳለ ሆኖ ያሳየው ያልተገባ ድርጊት መነሻነት በዳኞች እይታ ውስጥ አለመግባቱን ተከትሎ ተረፈ እንጂ የቀይ ካርድ ሰለባ ሊያደርገው የሚችልን ተግባር ነበር የፈፀመው።

ይህን አነሳን እንጂ መሰል ያልተገቡ ገለፍተኝነት የታከለባቸው ድርጊቶችን ሲፈፅም ተጫዋቹ የመጀመሪያው አይደለም። በፍሬው ደረጃ ለረጅም ጊዜያት በከፍተኛ ደረጃ የተጫወቱ ተጫዋቾች በዚህ ሁኔታ ደረጃቸውን የማይመጥን ምግባር ውስጥ መገኘታቸው በጣም የሚያስተዛዝብ እንደመሆኑ ከእንደዚህ ዓይነት አሉታዊ ጉዳዮች ራሱን ነፃ አድርጎ ከቆይታ በኋላ ያገኘውን የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ሆነ ክለቡን በሚገባ ደረጃ ለመጥቀም መታተር ይኖርበታል።

👉 የመስመር ተከላካዮች ጉዳይ

የክረምቱን የዝውውር መስኮት ሂደት በቅርበት ለተከታታለ በግራ እና ቀኝ የመስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ በጥቂት ተጫዋቾች ዙርያ የነበረው ርብርብ የሊጋችንን አሁናዊ ሁኔታ በደንብ የሚገልፅ ነው።

እርግጥ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች በሚያስብል ደረጃ የተጫዋችች ጥራት ችግር እንዳለ ቢታመንም በንፅፅር ከተመለከትናቸው ደግሞ በአንዳንድ የሜዳ ክፍሎች ያለው ውስንነት ይበልጥ ገኖ ይወጣል።

በእስካሁኑ የስድስት ሳምንት የሊጉ ጉዞ ውስጥ ከአዳማ ከተማው ሚሊዮን ሰለሞን ፣ ከድሬዳዋ ከተማው እንየው ካሳሁን ውጪ በጨዋታዎች ላይ ተፅዕኖ የፈጠረ የመስመር ተከላካይ ተሰላፊ ተጫዋች ማግኘት እጅጉን ከባድ ነው።

ዘመናዊ የመስመር ተከላካዮች በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ እንዲያበረከቱ የሚፈለገው ግልጋሎት ከፍ ማለቱ በራሱ ተጫዋቾችን የምንመዝንበት መስፈርቶች በርከት እንዲሉ ማስገደዱ በራሱ የፈጠረው ጫና እንዳለ ቢታመንም መሰረታዊ መመዘኛ በሆነው መከላከሉንም ማጥቃቱን በሚዛናዊነት መከወን በሚለው መመዘኛ አንፃር የአብዛኞቹ አፈፃፀም አመርቂ አይደለም።

ሲከላከሉ የነበሩት ቡድኑ ወደ ማጥቃት ሲሸጋገር የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም በሚያስችሉ ቦታዎች ላይ እጅጉን ዘግይቶ መገኘት በተመሳሳይ ደግሞ ሊያጠቁ የሄዱት የመስመር ተከላካዮች ደግሞ ቡድኑ ወደ መከላከል ሲሸጋገር እጅጉን ዘግይተው የመገኘታቸው ጉዳይ የመስመር ተከላካዮቻችን ላይ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያስገድዱ ናቸው።

ከላይ በጠቀስናቸው ሂደቶች ውስጥ “መች እና እንዴት” የሚሉት ጥያቄዎች የመስመር ተከላካዮቻችን በደንብ ሊያጤኗቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።