ቅድመ ዳሳሳ | ፋሲል ከነማ ከ ሲዳማ ቡና

በነገ ምሽቱ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።

ጨዋታው ከድል ጋር ከተገናኙ የሰነባበቱትን ሁለት ተጋጣሚዎች ያገናኛል። ብቸኛ ድሉን ሁለተኛው ሳምንት ላይ ያስመዘገበው ሲዳማ ቡና ከሀዋሳ ከተማው ሽንፈት በኋላ ከሦስት የ1-1 ውጤቶች በላይ ማስመዝገብ አልቻለም። ቻምፒዮኖቹ ፋሲል ከነማዎችም ጥሩ አጀማመር ያድርጉ እንጂ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን ብቻ አግኝተው ሊጉን በርቀት መምራት የሚችሉበትን ዕድል አምክነዋል። በመሆኑም ሁለቱም እጅግ አጥብቀው የሞፈልጉትን ድል ለማሳካት ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ተጋጣሚዎቹ ውጤቱን አጥብቀው የመፈለጋቸውን ጉዳይ ከመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው ተነስተን ስንመለከተው ነገም ከጎላ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይጠቁመናል። ከወላይታ ድቻ ነጥብ የተጋራው ፋሲል ከነማ በጨዋታው ይታይበት የነበረው በቶሎ ወደ ግብ የመድረስ ጥድፊያ ከዚሁ ውጤት ከማስመዝገብ ፍላጎት ጋር የተያያዘ ይመስላል። ይህ የስሜት መናር በነገው ጨዋታም ከተንፀባረቀ በተረጋጉ ቅብብሎች ተጋጣሚን የማስከፈት የጨዋታ ሂደቱ እና ዕድሎችን ወደ ግብነት የመቀየር ስኬቱን ሊያወርደው ይችላል። በተመሳሳይ ሲዳማ ቡናዎች በጊዜ መሪ መሆን ችለውበት በነበረው የአዳማው ጨዋታ ውጤቱን አጥብቆ ከመፈለግ የመነጨ የማፈግፈግ ባህሪን አሳይተው ነበር። ይህ ሁኔታ ነገ ከተደገመ ለተጋጣሚያቸው ሥነ ልቦና መነሳሳት እና ተደጋጋሚ ግቦችን ለማስተናገድ ሊዳርጋቸው ይችላል።

ፋሲል እና ሲዳማ የመስመር ጥቃታቸው ተዳክሞ መታየትም ሰሞኑን በተደረጉ ጨዋታዎች የሚያመሳስላቸው ሌላው ነጥብ ነው። የመስመር ተሰላፊዎቹ ጥምረት በተለይም በቀኝ በኩል በሜዳው ቁመት ያለው ጥምረት አስፈሪ የነበረው ፋሲል አሁን አሁን ተቀዛቅዞ እየታየ ነው። በሲዳማ ቡና በኩልም በድሬዳዋው ጨዋታ ፈንጥቆ የከሰመው የመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎ ዳግም ሊያንሰራራ አልቻለም። ምንአልባትም ለቡድኖቹ አጠቃላይ የማጥቃት ስትራቴጂዎች ስኬት መውረድ ይህ ነጥብ አንዱ መንስዔ ሳይሆን አይቀርም።

ከድቻ ጋር ወደ 4-4-2 ዳይመንድ የቀረበ አሰላለፍ የነበረው ፋሲል ሁለቱን ኮሪደሮች በመስመር ተከላካዮቹ ተሳትፎ በሚገባው ልክ አለመጠቀሙ ጥቃቱን ወደ መሀል እንዲጠብ አድርጎት ነበር። ቡድኑ አንድ አጥቂ ቀንሶ ወደ ቀደመ ቅርፁ የተመለሰበት ሂደት ጎል ባያስገኝለትም የተሻለ ሆኖ መታየቱ ነገም አምስት አማካዮችን ወደመጠቀም ወይንም በሦስት ተከላካዮች ጀምሮ የመስመር ተመላላሾቹን ሚና እንዲያጎላ ሊያደርገው ይችላል። ነገር ግን በሊጉ እስካሁን ብዙ ግብ (10) ያለው ፋሲል ያለግብ በወጣበት ጨዋታ ተሞክሮ ያልተሳካው የሁለት አጥቂዎች ጥምረት የሚደገም አይመስልም። ያ ከሆነ ደግሞ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ዕምነታቸውን ከጉዳት በተመለሰው ናይጄሪያዊው አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ላይ ሊጥሉ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ ነው።

ፊት መስመር ላይ ከተጋጣሚው ያነሰ አማራጭ ያለው ሲዳማ ቡና በይገዙ ቦጋለ እየተመራ እንደሚገባ ይጠበቃል። የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ግን አሁንም ብዙ ጉድለቶች ያለበት ሆኗል። ዳዊት ተፈራን ወደ አሰላለፍ በማምጣት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮች ቁጥር የመጨመር ስትራቴጂውም በአዳማው ጨዋታ የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም። ከአጥቂው ጀርባ በግራ እና ቀኝ የሚሰለፉት አማካዮች ከውጤት ማስጠበቅ ጋር በተያያዘ ከተጋጣሚ የግብ ክልል ርቀው መንቀሳቀሳቸውም በቀጥተኛ አጨዋወት ዕድሎች ሲፈጠሩ በቁጥር እየተመናመነ መልሶ ማጥቃቱ አቅም ሲያጣ ይታያል። በመሆኑም ቡድኑ የሜዳውን ስፋት የሚጠቀም እና የማጥቃት ጀብደኝነትን የቀላቀለ አቀራረብ ይዞ መግባት የሚያስፈልገው ጊዜ ላይ ያለ ይመስላል።

ፋሲል ከነማ አምበሉ ያሬድ ባየህን ከሁለተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት መልስ ሲያገኝ ሀብታሙ ተከስተ በቅጣት ሱራፌል ዳኛቸው በጉዳት ከቡድኑ ጋር አይኖሩም። በሲዳማ ቡና በኩል ጊት ጋትጉት እና ባለፈው መጠነኛ ጉዳት ገጥሞት የነበረው ሙሉዓለም መስፍን ከጉዳት ሲመለሱ የአማኑኤል እንዳለ መሰለፍ ግን አጠራጣሪ ሆኗል፡፡

ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት ለመምራት ኢምተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ስምንት ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ያላቸው ሲሆን ሁሉም ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀዋል። ተጋጣሚዎቹ ዕኩል አራት አራት ጊዜ ሲገናኙ ሲዳማ ቡና 11 ፋሲል ከነማ ደግሞ 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-3-2-1)

ሚኬል ሳማኬ

ዓለምብርሀን ይግዛው – አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንዳሻው – ከድር ኩሊባሊ

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – በረከት ደስታ

ኦኪኪ አፎላቢ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

ተክለማሪያም ሻንቆ

አማኑኤል እንዳለ – ግርማ በቀለ – ያኩቡ መሀመድ – ሰለሞን ሀብቴ

ብርሀኑ አሻሞ – ሙሉዓለም መስፍን

ሀብታሙ ገዛኸኝ – ፍሬው ሰለሞን – ብሩክ ሙሉጌታ

ይገዙ ቦጋለ