“አስቀድሞ የብሔራዊ ቡድኑን ጨዋታዎች ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የወጣው መርሐ-ግብር ይቀጥላል” አቶ ክፍሌ ሰይፈ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ቀድሞ ይቋረጣል ወይ? የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ለሶከር ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጥተዋል።

የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጅማሮውን በሀዋሳ በማድረግ በደመቀ ሁኔታ እየተደረገ እንደሆነ ይታወቃል። ሊጉም ባለንበት ሳምንት የሰባተኛ ሳምንት መርሐ-ግብሮችን እያስተናገደ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ከሊጉ ክለቦች ዋና እና ረዳት አሠልጣኞች ጋር ውይይት እንዲያደርጉ አክሲዮን ማኅበሩ ለክለብ ዋና እና ረዳት አሠልጣኞች ጥሪ እንዲያቀርብለት ደብዳቤ መፃፉ ይታወሳል። በቀረበው ጥሪ መሠረትም ከትናንት በስትያ የክለቦቹ ዋና እና ረዳት አሠልጣኞች በሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ውይይት ያደረጉ ሲሆን ለብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ መዘጋጃ ጊዜ እንዲሆንም ሊጉ ቀድሞ ከሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በኋላ እንዲቋረጥ ሀሳብ አንፀባርቀው አቋም ይዘው መውጣታቸውን ዘግበን ነበር።

የክለብ አሠልጣኞቹ የያዙትን አቋም (በይፋ ለአክሲዮን ማኅበሩ አለማስገባታቸው ልብ ይሏል) ተከትሎ ሊጉ ይቋረጣል ወይስ በተያዘለት መርሐ-ግብር መሰረት እስከ ዘጠነኛ ሳምንት ይቀጥላል የሚለው ጉዳይ ትናንት እና ዛሬ መነጋገሪያ ሆኖ የነበረ ሲሆን ጉዳዩን እንዲያጠሩልንም ሊጉን በበላይነት የሚያስተዳድረውን አክሲዮን ማኅበር በሥራ-አስኪያጅነት የሚመሩት አቶ ክፍሌ ሰይፈን አግኝተን ተከታዩን ሀሳብ ተቀብለናቸዋል።

“እኛ የሊጉን መርሐ-ግብር ስናወጣ ዝም ብለን አይደለም። በተጠና ሁኔታ ያሉትን ነባራዊ ጉዳዮች ባማከለ መልኩ ነው። ገና ቀድሞ መርሐ-ግብሩ ሲወጣም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር እና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ታሳቢ አድርገናል። አሁን ከአሠልጣኞች ተነሳ የሚባለውን ነገር በሚዲያ (ሶከር ኢትዮጵያ ላይ) ነው ያየሁት። ሊግ ዝም ብሎ አይቋረጥም። ከምንም በላይ ደግሞ ከቀጥታ ስርጭት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ትላልቅ ጥያቄዎች አሉ። በጣም አስገዳጅ ነገሮች ካልመጡ በስተቀር መርሐ-ግብሮቹ አይነኩም። አይደለም ሊጉን ማቋረጥ ቀድሞ 9 ሰዓት የተባለን ጨዋታ እንኳን 12 ሰዓት ማድረግ አይቻልም። ስለዚህ ቀድሞ የብሔራዊ ቡድኑን ጨዋታዎች ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ የወጣው መርሐ-ግብር ይቀጥላል።” በማለት አጠር ያለ መልስ ሰጥተውናል።

ይህንን ተከትሎ አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሊግ እርከን የሆነው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሰባተኛ ሳምንት በኋላ ሁለት የጨዋታ ሳምንታትን በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም አከናውኖ ታህሳስ 15 የሚቋረጥ ይሆናል።