“ወደ ካሜሩን እሄዳለው ብዬ አስባለሁ” – በረከት ደስታ

በያዝነው የውድድር ዓመት ጥሩ መነቃቃት ከሚታይባቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ከሆነው በረከት ደስታ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።

ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የሚያሳዩት ጥረት በግቦች ላይ በሚያደርጓቸው ተሳትፎዎች ይገለፃል። ሲሳካላቸው እና ለቡድናቸው ግብ ሲያስቆጥሩ አልያም ግብ የሆነ ኳስ ሲያመቻቹ በቶሎ ዓይን ውስጥ ይገባሉ። ከዚህ ውጪ ግን በአጠቃላይ የቡድኑ መዋቅር ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ መሄዱ ለአሰልጣኝ ቡድን አባላት ወይም በቅርበት ለተከታተላቸው ብቻ ግልፅ የሚሆን እውነታ ነው። የዛሬው እንግዳችን በዚህ ረገድ የሚነሳ ነው። በአዲሱ ቡድኑ ውስጥ ያለው ተፅዕኖ ፈጣሪነት እየጎላ መጥቶ በቅርብ ሳምንታት ደግሞ ግብ በማስቆጠር እና በተለይም የመጨረሻ ኳሶችን በማመቻቸት ጎልቶ እየወጣ ይገኛል ፤ የፋሲል ከነማው የመስመር ተጫዋች በረከት ደስታ።

የሻሸመኔ ፍሬ የሆነው በረከት ከፕሮጀክት ጅማሮው በኋላ 2008 ላይ በአዳማ ታዳጊ ቡድን ውስጥ መካተት ችሎ ነበር። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ለዋናው ቡድን መጫወት የጀመረ ሲሆን እስከ 2012 ድረስም በአዳማ ቆይቷል። ተጫዋቹ በመቀጠል ወደ ፋሲል ከነማ ያመራ ሲሆን ከቡድኑ ጋር ቻምፒዮን ሆኖ ሁለተኛ ዓመቱን በጥሩ ሁኔታ መጀመር ችሏል።

በሰባቱ ሳምንታት ውስጥ አንድ ግብ አስጥሮ ሦስት ለግብ ማመቻቸት የቻለው በረከት በፋሲል የነበረው አጀማመር ቀላል አልነበረም። ወደ ዋና አሰላለፍ ውስጥ በቋሚነት መግባት አለመቻሉ ሲታይ ቡድኑ ለሁለተኛ ዕቅድነት አስቦ ያስፈረመው ይመስል ነበር። ሆኖም በአፄዎቹ ቤት በአምናው የውድድር ዓመት በሂደት ቁልፍ ተጫዋች መሆን ችሏል። ዘንድሮ ደግሞ ይበልጥ ጎልብቶ እየታየ በሁሉም ጨዋታዎች በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ሲካተት ትርጉም ያለው እንቅስቃሴም እያደረገ ነው። በረከት የዚህ መሻሻል ሚስጥር ከቡድኑ ጋር መላመድ ነው ይለናል። “የሚታይብኝ መነቃቃት ምክንያቱ ከቡድኑ ጋር መላመዴ ነው። አምና ስለፈረምኩኝ ብዙም አልተላመድኩ ነበር። ወጣ ገባ ነበር የዓምናው አጨዋወቴ። ዘንድሮ ግን ከጅምሩም ጥሩ ዝግጅት ስላደረግኩ ያ ነገር ነው መነቃቃት እንዲኖረኝ ያደረገው።”

በእርግጥም ፋሲል ከነማ በሽመክት ጉግሳ በሚመራው መስመር ላይ አድልቶ ሲያጠቃ ይታይ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ የበረከት በጥሩ አቋም ላይ መገኘት ቡድኑ በሁለቱም መስመሮች ስል እንዲሆን አስችሎታል። በረከት በዚህ መጠን አስተዋፅዖው ማደጉ ብቻ ሳይሆን የዘንድሮ ለውጡ የባህርይም ጭምር ሆኖ ይታያል። ሜዳ ላይ ያለው እልሁ ከተጫዋቾች ጋር ብቻ ሳይሆን ከደጋፊዎች ጋር እስከመጋጨት ያደረሰው የመስመር አጥቂው አሁን ላይ ምራቁን ዋጥ ያደረገ ይመስላል። “የዚህ ምክንያት አንደኛ ቤተሰብ ከመመስረቴ ጋር ይያያዛል። ከዚህ በፊት ከተጫዋቾች ጋር እጋጭ ነበር፤ በጣም ስሜታዊ እሆን ነበር። አሁን ግን ይህን ነገር አጥፍቼ አዲሱ በረከት ለመሆን ስለፈለግኩ ስሜታዊነቴን ቀንሼ እየተጫወትኩ እገኛለሁ።” ሲልም የመሻሻሉን ምክንያት ያስቀምጣል።

በሀገራችን እግርኳስ ተጫዋቾች በየዓመቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ ያሉበትን ወቅታዊ አቋም ከግንዛቤ ውስጥ ያላካተቱ ዝውውሮችን ሲፈፅሙ ይታያል። ይህም የእግርኳስ ህይወታቸው እንዳይረጋጋ መንስኤ መሆኑ ግልፅ ነው። በረከት ከአሳዳጊ ክለቡ ያደረገው ብቸኛ ዝውውር ወደ ተረጋጋ አደረጃጀት ያለው ፋሲል ከነማ መሆኑ ሳይጠቅመው አይቀርም። ተጫዋቹ ግን በዚህ ዙሪያ ተመጣጣኝ ምክንያት በማስቀመጥ በአንድ ክለብ በመርጋት እና ክለብ መቀየርን ያነፃፅራል። “ክለብ ቶሎ ቶሎ አለመቀየር መልካም ጎኑ የቡድኑን ባህሪ እንድታውቅ ያደርግሀል። ክለብ መቀያየርም በእርግጥ በራሱ ጥፎ ነገር አይደለም። ራስህን የማየት ዕድል ይሰጥሀል። አንድ ቡድን ውስጥ ብዙ ስትቆይ የመጀመሪያውን ችሎታህን ይዘህ ልትቀጥል እና አዲስ ነገር ላትፈጥር ትችላለህ። አዲስ ክለብ ሲሆን አዲስ ነገር ስለሚጠበቅም በሥራህ ላይ አዲስ ተነሳሽነት ይፈጥራል። እኔ አዳማ ስላደኩ ከደግኩ በኋላም ሁለት ዓመት የማገልገል ግዴታ ነበረብኝ። ከዛ ግን ክለብ መቀየሬ ለእኔ ጥሩ ነገር ሆኖልኛል።”

የመስመር አጥቂው ከሀዲዱ ወጣ ያለ መስሎ በዚህ ሳምንት ወደ አሸናፊነት የተመለሰው የእግርኳስ ህይወቱ ሁሉተኛ ክለብ ዳግም ቻምፒዮን እንደሚሆንም ያስባል።” ዘንድሮም ግስጋሴያችን እስከዋንጫው ነው ፤ ድጋሚ ዋንጫ እናነሳለን ብዬ አስባለሁ። ቡድኖች ሁሉ ጠንክረው ነው የመጡት ፤ የዘንድሮው ውድድር ጠንካራ ነው። ብዙዎቹ ከእኛ ጋር ለመከላከል ነው የሚመጡት። ወደ ፊት ገፍቶ ለመጫወት አይደለም የሚመጡት። ቡድናችን ግን አሁን ወደማሸነፍ መንፈስ ከመጣ እስከዋንጫ እንሄዳለን ብዬ ነው የማስበው።”

ይሁን እንጂ በአዳማ ከተማ እያለ 2010 ላይ ራሱ በረከትን ጨምሮ እንደምኞት ፣ ሙጂብ ከነዓን ፣ ሱራፌል ፣ ዳዋ ፣ ቡልቻ ፣ ሱለይማን እና ሌሎች አሁን በሊጉ ላይ በጥሩ ሁኔታ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ተጫዋቾችን የያዘው ቡድን እንደአሁኑ ክለቡ ሁሉ ለቻምፒዮንነት የሚጫወት እንደነበር ያምናል። “2010 ላይ የነበረው አዳማ ለዋንጫ የሚጫወት እና ትልቅ ትኩረት የነበረው ቡድን ነበር። ከበጀት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ነው አጨራረሱ ያላማረው። ከአሁኑ የፋሲል ቡድን ጋር በእልኸኝነቱ እና ለማሸነፍ ያላቸው ሞራል ያመሳስላቸዋል። ተነሳሽነታቸው በጣም ይመሳሰላል። ጥሩ በሆኑበትም ባልሆኑበትም ጊዜ ውጤት ይዘው ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት ያመሳስላቸዋል።” ይላል።

በረከት ከዛ የአዳማ ቡድን ወደ ፋሲል ከነማ ከመጣ በኋላ እንደተጫዋች ተለውጦ ከታየባቸው ነጥቦች ሌላኛው በታታሪነት ሰፊ የሜዳ ክፍል ለመሸፉን የሚያሳየው ጥረት እና የቡድን ተጫዋች እየሆነ የመምጣቱ ነገር ነው። በዚህም ከመስመር አጥቂነት ይልቅ ወደ አማካይነቱ በማድላት የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ሲያመችልች ይታያል። ግብ ማስቆጠር እና ማመቻቸትን ሲያነፃፅርም “ሳነፃፅረው ራስ ከማስቆጠር ይልክ ለጓደኛህ አቀብለህ ሲቆጠር ትልቅ ደስታ አለው። እርካታውን ታየዋለህ ፤ ጓደኛህ ሲደሰት ማየት በጣም ደስ ያሰኛል። በእርግጥ በብዛት ጎል የሚያገባ ሰው ነው የሚፈለገው። አሁን አሁን ነው እየተለመደ የመጣው። ጎል ከሚያገባው ይልቅ የሚሰጥው ሰው እየተወደደ መምጣት ጀምሯል። መሻሻል አለ ማለት ይቻላል። እኔ የምለው ግን ኳስ ሲሰጥ ይበልጥ ደስ ይላል ነው።”

ተጫዋቹ በመልካም አቋም ላይ የተገኘበት ጊዜ ይበልጥ ትከረትን ይስባል። ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰችበት የውድድሩም መጀመሪያ የተቃረበበት ወቅት መሆኑ ነው። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስር አንድ ጊዜ የመመረጥ ዕድል የነበረው ተጫዋቹ በዚህ ዙሪያ ላቀረብንለት የመጨረሻ ጥያቄ ይህንን ብሎናል። “እኔ ስለዚህ ነገር ማውራት ብዙ አልፈልግም ፤ አሰልጣኝ የሚወስነው ነው። ወደ ካሜሮን እሄዳለው ብዬ አስባለሁ። ዋናው ሜዳ ላይ የሚታይ ነገር ነው። ካልሆነም እዚሁ ሥራዬን እሰራለሁ። እኔ የመሄዱ ሀሳብ አለኝ ፤ እንደ አሰልጣኙ ግን ይወሰናል። እሱ የሚፈልገው አጨዋወት አለ ፤ ለዛ የማልሆን ከሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም።”