የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ የመክፈቻ ጨዋታዎች ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሐ የ2014 የውድድር ዘመን ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ ሀምበሪቾ እና መድን ድል ቀንቷቸዋል።

ረፋድ 4፡00 ላይ የተካሄደው የመክፈቻ ጨዋታ በፌዴራል ፖሊስ እና ጅማ አባ ቡና መካከል የተደረገ ነበር። የጅማ ከተማ ከንቲባ ነጂብ አባዲጋ፣ ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው እና የውድድር ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁን ጨምሮ ሌሎች የክብር እንግዶች ተገኝተው ያስጀመሩት ጨዋታ ጥሩ ድባብ የታየበት ቢሆንም ጎል ሳይቆጠርበት 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከሰዓት በኋላ በምድቡ ጠንካራ ግምት ከተሰጣቸው ቡድኖች አንዱ የሆነው ሀምበሪቾ እና አቃቂ ቃሊቲን ያገናኘው የ8፡00 ጨዋታ በሀምበሪቾ 1-0 አሸናፊት ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ ምንም ግብ ያላሳየው ጨዋታ ከእረፍት መልስ የቀድሞ የፌዴራል ፖሊስ እና ኢትዮጵያ ቡና አጥቂ ሰይፈ ዛኪር በ65ኛው ደቂቃ ከመረብ ጋር ባገናኘው ብቸኛ ጎል ሀምበሪቾ 1-0 አሸንፎ ሊወጣ ችሏል።

የዕለቱ የመጨረሻ የምድቡ ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ሶዶ ከተማ መካከል የተደረገ ነበር። ያለግብ ረጅም ደቂቃዎችን ባሳለፈው ጨዋታ ተስፋዬ ታምራት በ70ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ብቸኛ ግብ መድን ሦስት ነጥብ ማሳካት እንዲችል አድርጓል።

የምድቡ ቀጣይ የአንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ በ8፡00 እና 10፡00 ሲቀጥል ጉለሌ ክ/ከተማ ከየካ ክ/ከተማ፥ ነቀምቴ ከተማ ከ ደቡብ ፖሊስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።