ቅድመ ዳሰሳ | አርባምንጭ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር

የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ቀዳሚውን ጨዋታ የተመለከቱ ሀሳቦችን እንዲህ አንስተናል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች የውድድር ዓመቱን በተመሳሳይ ሁኔታ በሽንፈት ነበር የጀመሩት። ከዚያ ወዲህ የመጡት ሳምንታት ግን ወደተለያዩ መንገዶች ወስደዋቸዋል። አርባምንጭ ከተማ ራሱን ከሽንፈት ጠብቆ ከዘጠኝ ነጥቦች ጋር ለነገው ጨዋታ ሲደርስ ጅማ አባ ጅፋር ግን አሁንም ከመጀመሪያ ነጥቡ ጋር አልተገናኘም። ቡድኖች ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ በማይገፅ መልኩ ድንገት ተቀይረው የሚታዩበት ሊጉ ነገስ በዚህ ጨዋታ ምን ይዞ ይመጣል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ይሆናል።

አርባምንጭ ከተማ በመጨረሻ ጨዋታው ባልተሟላ ተጫዋች ካገኘው ወልቂጤ ከተማ ሙሉ ነጥብ አለማሳካቱ ትኩረት የሚስብ ነበር። ቡድኑ በተለይ ጨዋታውን ሲጀመር የነበረው የተነሳሽነት ደረጃ ከወትሮው ወረድ ብሎ የነበረ መሆኑ ለነገውም ጨዋታ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው። ምንም እንኳን ውጤት ከራቀው ቡድን ጋር ቢገናኝም ይህ ድክመት ከተደገመ ዋጋ ሊያስከፍለው የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው። በጅማ በኩል ደግሞ ከዚህ የተለየ እውነታን እናገኛለን። በባህርዳሩ ሽንፈት ቡድኑ በጨዋታ እንቅስቃሴ እና በማጥቃቱ ረገድ የነበረው ብልጫ ብቻ ሳይሆን ውጤት ይዞ ለመውጣት በተሰላፊዎቹ ላይ ይነበብ የነበረው መነሳሳት የነገን ጨምሮ ለቀጣይ ጨዋታዎች ሊያስቀጥለው የሚገባው ጠንካራ ጎኑ ነበር።

ከላይ ከተነሳው ሀሳብ ጋር በተያያዘ የአርባምንጩ አጥቂ ኤሪክ ካፓይቶ በወልቂጤው ጨዋታ የነበረው አፈፃፀም መውረድ ለአሰልጣኝ መሳይ የሚዋጥ አልነበረም። ዝርግ 4-4-2ን ምርጫው ያደረገው ቡድን የፊት አጥቂዎቹን ጫና የመፍጠር ብቃት አብዝቶ ይሻል። ከሊጉ መክፈቻ ሽንፈት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ሳያስቆጥር መውጣቱም እዚህ ቦታ ላይ በትኩተት እንዲያስብ የሚያነሳሳ ነጥብ ነው። በነገው ጨዋታ ከተጋጣሚው የመከላከል ድክመት አንፃር ከኳስ ውጪ ከበድ ያለ ጫናን መፍጠር እና ኳሶችን ማቋረጥ ስለሚኖርበትም አሰልጣኙ ለበላይ እና ፍቃዱ ጥምረት ቅድሚያ ሊሰጡ ይችላሉ። ሲያጠቃ የሜዳውን ስፋት አብዝቶ የሚጠቀም እና መሀል ላይም ከሚቋረጡ ኳሶች ቀጥተኛ ጥቃቶችን ለመሰንዘር የሚጥር ቡድን ከአዞዎቹ ይጠበቃል።

የጅማ አባ ጅፋር የሜዳ ላይ ተጋጣሚው የዕለቱ ተቃራኒ ቡድን ብቻ ሳይሆን የእስካሁኑም ውጤቱ ጭምር ነው። ከማሸነፍ ውጪ ምንም አማራጭ የሌለው በመሆኑ ሁሉንም ነገር ወደፊት ለመወርወር መጣሩ አይቀርም። እርግጥ ነው ከውጤት ውጪ ቡድኑ በመዋቅር ደረጃ በተለይም በሚያጠቃበት መንገድ ለውጦች እየታዩበት ነው። ነገር ግን የማሸነፍ ግዴታው ለመሀል ሜዳ ቀርቦ የሚንቀሳቀስ የኋላ መስመሩን ክፉኛ ለመልሶ ማጥቃት ሲዳርገው ይስተዋላል። ነገም ቀጥተኛ አጨዋወትን ምርጫው ያደረገው ተጋጣሚው በዚሁ መንገድ ሊጎዳው የመቻሉ ዕድል ሰፊ ነው።

ከዚህ ባለፈ የጅማ አባ ጅፋር የማጥቃት ሂደት ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አቅሙ ይጅግ ሊሻሻል ይገባዋል። ጫና ፈጥሮ ተጋጣሚ ሳጥን ደርሶ ኳሶችን ማባከን በራሱ ለፈጣን ጥቃት በር ከፋች መሆኑ የቅብብል ጥራቱን ከፍ የማድረግ ግዴት ይጥልበታል። የአርባምንጭ ከተማ አማካዮች የእንዳልካቸው እና አንዷለም የረጋ የመሀል ጥንረት ሲታሰብ ደግሞ ጅማዎች ሰብሮ ለመግባት መስመሮችን የተሻለ አማራጭ አድርገው ሊወስዱ እንደሚችሉ ፍንጭ ይሰጣል። ተሳክቶለት ወደ ግብ አፋፍ ከደረሰስ ከሙከራዎች ጭምር የራቁት አጥቂዎቹ የመጨረስ ብቃት ምን ላይ ነው የሚለው በራሱ በነገው ጨዋታ ምላሽ የሚሻ ነጥብ ነው።

አርባምንጭ ከተማ አሸናፊ ፊዳን በቅጣት አብነት ተሾመ ደግሞ በጉዳት ያጣል። በአንፃሩ ፀጋዬ አበራ ከጉዳት ሲመለስ በመጨረሻው ጨዋታ በጡንቻ ህመም ያልነበረው ሳምሶን አሰፋንም ዳግም ማግኘቱ ተጨማሪ መልካም ዜና ሆኖለታል። አሰልጣኝ መሳይ ጥሩ በተነቀሳቀሰው ግብ ጠባቂ ይስሀቅ ተገኝ ይቀጥላሉ ወይስ ወደ ዋና ተመራጫቸው ፊታቸውን ያዞራሉ የሚለውን የነገ የአሰላለፍ ምርጫቸው ይጠቁመናል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ግን የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና አልተሰማም።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ ዓባይነህ ሙላት በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለት ጊዜ ተገናኝተው (2010) አባ ጅፋር የመጀመርያውን በኮኪኪ ሐት ትሪክ 3-1 ሲያሸንፍ ሁለተኛውን ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደስ አበበ – በርናንድ ኦቺንግ – ማሪቲን ኦኮሮ – ሙና በቀለ

ሀቢብ ከማል – እንዳልካቸው መስፍን – አንዱዓለም አስናቀ – ሱራፌል ዳንኤል

በላይ ገዛኸኝ – ፍቃዱ መኮንን

ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)

አላዛር ማርቆስ

ሽመልስ ተገኝ – አሳሪ አልመሀዲ – የአብስራ ሙሉጌታ – ወንድምአገኝ ማርቆስ

ሮጀር ማላ – መስዑድ መሀመድ

ዱላ ሙላቱ – ምስጋናው መላኩ – መሐመድ ኑርናስር

ዳዊት ፍቃዱ