ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ – የሶከር ኢትዮጵያ ሰባተኛ ሳምንት ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን በከፍተኛ ትኩረት ለአምባቢዎች የምታቀርበው ሶከር ኢትዮጵያ የሰባተኛ ሳምንት ምርጥ ቡድንን በሚከተለው መልኩ መርጣለች።

የተጫዋች አደራደር ቅርፅ 4-1-4-1

ግብ ጠባቂ

አላዛር ማርቆስ – ጅማ አባጅፋር

ወጣቱ የግብ ዘብ አላዛር ጅማ አባጅፋር ከአርባምንጭ ከተማ ጋር አቻ ሲለያይ ያሳየው ብቃት ድንቅ ነበር። ከወትሮው በተለየ ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ሲጥሩ የነበሩት ጅማዎች ተከላካዮቻቸው ወደ መሐል ሜዳ ተጠግተው ሲጫወቱ የተውትን ሰፊ ቦታ ተጋጣሚዎች እንዳይጠቀሙት በጥሩ የሰዓት አጠባበቅ እየወጣ ሲከላከል ከመሆኑ በተጨማሪም የአርባምንጭ ተጫዋቾች ያደረጓቸውን ጥሩ ጥሩ የአየር ላይ እና የመሬት ላይ ኳሶች ሲያመክን ስለነበር በምርጥ ቡድናችን ቦታ አግኝቷል።

ተከላካዮች

ዓለምብርሀን ይግዛው – ፋሲል ከነማ

ወጣቱ የመስመር ተጫዋች ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በተካተተበት ጨዋታ 76 ደቂቃዎችን ሜዳ ላይ አሳልፏል። ከፍ ያላ የማጥቃት ተሳትፎን በማድረግ በአዲሱ የመስመር ተከላካይነት ሚና ላይ እየደመቀ የመጣው ዓለምብርሀን ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገችውን ግብ አስቆጥሯል። ምንም እንኳን ተጫዋቹ ተገቢ ያልሆነ የሜዳ ላይ ባህሪ ቢያሳይም በሳምንቱ በየቡድኑ በቦታው ከተመለከትናቸው ተጫዋቾች አንፃር ያሳየው ብቃት ተመራጭ አድርጎታል።

ቃለአብ ውብሸት – ሀዲያ ሆሳዕና

በሦስት ተጫዋቾች በተዋቀረው የሀዲያ ሆሳዕና የኋላ ክፍል ውስጥ የቀኙን ቦታ የመሸፈን ኃላፊነት የነበረው አምና ወደ ዋናው ቡድን ያደገው ወጣቱ ተከላካይ ድንቅ ቀን አሳልፏል። ተጫዋቹ ከተጋጣሚያቸው መከላከያ በረጅሙ ይላኩ የነበሩ ለስህተት የሚጋብዙ ኳሶችን ይቆጣጠር የነበረበት መንገድ እና ስኬታማ የነበሩት ሸርተቴዎቹ ቡድኑን ከጥቃት ከመከላከል ባለፈ ከዕድሜው በላይ እየበሰለ መሆኑን የሚያስረዱ ነበሩ።

የአብስራ ሙሉጌታ – ጅማ አባ ጅፋር

በደካማው የቡድኑ የመከላከል መዋቅር ውስጥ በግሉ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው ወጣቱ ተከላካይ አርባምንጭን በገጠሙበት ጨዋታም ይህንኑ ብቃቱን ደግሞታል። በአራት ተከላካዮች ጀምሮ ወደ ሦስት ተከላካይ መስመር በተቀየረው ጅማ ውስጥ ራሱን አስማምቶ የኋላ መስመሩን በብስለት መምራት ችሏል። ወደ መሀል ሜዳ በተጠጋው የመከላከል ስትራቴጂው ላይ የተረጋጋው የአብስራ መኖር የመልሶ ማጥቃት ተጠቃሚ የነበረው ተጋጣሚያቸውን አደጋ ቀንሶታል።

አምሳሉ ጥላሁን – ፋሲል ከነማ

በእስካሁኑ የሊጉ ጅማሮ በቅጣት ካመለጡት ጨዋታዎች ውጪም በቀደመ ብቃቱ ልክ ሲንቀሳቀስ ያልነበረው አምሳሉ በሲዳማው ጨዋታ ሰምሮለት ታይቷል። የተጋጣሚውን የመስመር ጥቃት ከማፈን ባለፈ እንደወትሮው በጀብደኝነት በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ ሲሳተፍ ተመልክተነዋል። ይህ ጥረቱንም ግብ በማስቆጠር ያጀበው መሆኑም በግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ያለከልካይ ተመራጭ እንዲሆን አስችሎታል።

አማካዮች

ተስፋዬ አለባቸው – ሀዲያ ሆሳዕና

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወጥ አቋም እያሳዩ ከሚገኙ ተጫዋቾች ውስጥ ግዙፉ የተከላካይ አማካይ ተጠቃሽ ነው። በመከላከያው ጨዋታ የቡድን ጓደኞቹን ከኳስ ውጪ በማስተባበር ጭምር ከተከላካዮች የሚፈለገውን ሽፋን ሲሰጥ አምሽቷል። አስፈሪ ጥቃቶችን ከማቋረጥ ባለፈ የቡድኑን ማጥቃት ከቦታው ላይ የመራበት መንገድ እና በጨዋታ ይነበብበት የነበረው በራስ መተማመን ከውጤት ሮቆ ለቆየው ቡድን ከድል ጋር መገናኘት ከፍ ያለ ድርሻ ነበረው።

በረከት ደስታ – ፋሲል ከነማ

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት የነጠረ ብቃት ካሳዩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ በረከት ነው። ቡድኑ ፋሲል ሲዳማ ቡናን አራት ከምንም ሲረታ በሦስቱ ጎሎች ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ነበር። ሁለቱን አመቻችቶ በማቀበል አንዱን በማስቆጠር። ከዚህ ውጪ አልፎ አልፎ ብቻ በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ የሚጫወተው ምንተስኖት ከበደ ተፈጥሯዊ ቦታው አለመሆኑን በመጠቀም ተደጋጋሚ የኳስ ንክኪዎችን በማድረግ የቡድኑን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲዘውር ነበር።

ፍፁም ዓለሙ – ባህር ዳር ከተማ

ባህር ዳር በደረጃ ሰንጠረዡ መሻሻል ያገኘበትን ድል ወላይታ ድቻ ላይ ሲያገኝ የፍፁም ብቃት አስፈላጊ ነበር። በ4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፍ ወደ ሜዳ በገባው ቡድን ውስጥ ከአጥቂ ጀርባ ያለውን ቦታ ይዞ የተጫወተው ፍፁም በመስመሮች መካከል እየተገኘ ለአጥቂዎቹ ኳሶችን ከማመቻቸት ባለፈ በዛው ቦታ ተገኝቶ ካልታሰበ ቦታ እንዲሁም ከተከላካዮች አፈትልኮ በመውጣት ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ ሦስተኛውን የዓሊን ጎል እንዲገኝ አመቻችቶ አቀብሎ ጥሩ የጨዋታ ቀን አሳልፏል።

በቃሉ ገነነ – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ሰበታን ሲረታ በአማካይ መስመሩ ላይ ጥንካሬ አላብሶ ሲንቀሳቀስ የነበረው በቃሉ ገነነ ሌላኛው በመሐል ሜዳው የመረጥነው ተጫዋች ነው። በተለይ ተጫዋቹ የተሰጠውን ከሳጥን ሳጥን የመሮጥ ሚና በሚገባ ሲወጣ ያስተዋልን ሲሆን በሁለቱም የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች በሰዓቱ እየተገኘም ቡድኑ ጎል እንዳያስተናግድ እና እንዲያስቆጥር ሲታትር ነበር። ሦስተኛውንም የመስፍን ታፈሰ ጎል አመቻችቶ አቀብሏል። ከዚህ ውጪ በአምስት የአማካይ ተጫዋቾች የገቡት ሰበታዎች በመሐል ሜዳው ላይ ብልጫ እንዳይኖራቸው ሲጥር ተመልክተነዋል።

ኢያሱ ታምሩ – ሀዲያ ሆሳዕና

በአሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ዕምነት ተጥሎበት በቀዳሚ የአሰላለፍ ምርጫ ውስጥ የቀጠለው ኢያሱ ልዩነት የፈጠረበትን የጨዋታ ዕለት አሳልፏል። የመስመር ተመላላሽነት ጨዋታውን የከወነው ኢያሱ የወትሮው አስገራሚ ታታሪነቱ ሳይዛነፍ በግራው ኮሪደር ላይ ሲመላለስ አርፍዷል። ይህም የማጥቃት ጥረቱ ፍሬ አፍርቶ ቡድኑን አሸናፊ ያደረጉትን የሀብታሙ ታደሰን ሁለት ግቦች አመቻችቶ አቀብሏል።

አጥቂ

ሀብታሙ ታደሰ – ሀዲያ ሆሳዕና

ሆሳዕና የዓመቱን የመጀመሪያ ድል ሲያገኝ ሁለቱን ግቦች በሁለቱ አጋማሾች ከመረብ ያገናኘው ሀብታሙ ምርጥ ቡድናችን በአጥቂነት እንዲመራ አድርገነዋል። ከባዬ ገዛኸኝ ጋር ተጣምሮ ሸጋ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ሀብታሙ የቡድኑን የማሸነፊያ ግቦች ከማግባቱ ባለፈ ለወትሮ ጠጣር የነበረውን የመከላከያን የኋላ መስመር በፈጣን እንቅስቃሴዎቹ በማሸበት እሱ እና የቡድን አጋሮቹ ክፍተቶችን እንዲያገኙ ሲጣጣር ነበር። ከዚህ ውጪ ከአንድ የአጥቂ ተጫዋች የሚጠበቁትን የቦታ አያያዝ፣ የሰዓት አጠባበቅ እና የአጨራረስ ብቃት አሻሽሎ መታየቱ በቦታው ተመራጭ እንዲሆን አስችሎታል።

አሰልጣኝ

አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ሳምንቱ ከመጀመሩ በፊት ሊጉን ይመራ ከነበረው ወላይታ ድቻ ጋር የተገናኘበትን ጨዋታ ከእንቅስቃሴ ብልጫ በማሳየት ጭምር ቡድናቸውን ለድል አብቅተዋል። በመልሶ ማጥቃት አስፈሪ ሆኖ የሰነበተው ወላይታ ድቻን እንደልብ ከሜዳው እንዳይወጣ በማድረግ ጨዋታውን በፈለጉት መንገድ አስኪደው በሁለት ግብ ልዩነት ያሸነፉበት ዕቅዳቸው የሳምንቱ ኮከብ አሰልጣኝ አድርጓቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ያሬድ በቀለ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ቴዎድሮስ በቀለ (ኢትዮጵያ ቡና)
ደስታ ዮሐንስ (አዳማ ከተማ)
መስዑድ መሐመድ (ጅማ አባጅፋር)
አሜ መሐመድ (አዳማ ከተማ)
አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)
መስፍን ታፈሰ (ሀዋሳ ከተማ)