​በቅዱስ ጊዮርጊስ አሠልጣኝ ስንብት ዙሪያ ምን ተባለ?

👉”ይሄ አሠልጣኝ (ክራምፖቲች) ከመጣ በኋላ አምስት እና ስድስቴ ደብረዘይት ለማስማማት ሄደናል።”

👉”ሀገር ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች ከውጪ ካመጣናቸው አሠልጣኞች ጋር አይግባቡም።”

👉”ሄኖክ አዱኛን ከሜዳ ሲወጣ አልሳቀም ብሎ ነው የቀጣው። አንዱን ደግሞ…”

👉”በአንድ ወቅት ተጫዋቾቹን ለማስተማር ሞከርን። በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ማታ ማታ እንዲማሩ አደረግን። ግን…”

በኢትዮጵያ እግርኳስ ገናና ስም ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዛሬው ዕለት በቅሎ ቤት አካባቢ በሚገኘው የመዝናኛ ማዕከል አስተዳደራዊ መዋቅሩን ለማዘመር ከድንቅ ኢትዮጵያ ብራንዲንግ ጋር ስምምነት እንደፈፀመ ከሰዓታት በፊት ዘግበን ነበር። በስምምነት መርሐ-ግብሩ ላይ ስለ ጉዳዩ መግለጫ ከመሰጠቱ ባለፈ ከስፍራው ከተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት በቅርቡ የተሰናበቱትን ሰርቢያዊ አሠልጣኝ ዝላትኮ ክራምፖቲች ስንብት በተመለከተ የክለቡ ፕሬዝዳንት አቶ አብነት ገብረመስቀል ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“እኛ ሀገረ  ትልቅ አሠልጣኝ አይመጣም። ከመጫወቻ ሜዳ ጀምሮ እኛ ሀገር ያለው ችግር ከባድ ነው። ከዚህ ውጪ እኛ ሀገር ያሉት ተጫዋቾች ከውጪ ካመጣናቸው አሠልጣኞች ጋር አይግባቡም። ሁሌ ጥል አለ። ሁል ጊዜ ማስታረቅ እና ማግባባት አድካሚ ነው። ይሄ አሠልጣኝ (ክራምፖቲች) ከመጣ በኋላ አምስት እና ስድስቴ ደብረዘይት ለማስማማት ሄደናል።

“ሄኖክ አዱኛን ከሜዳ ሲወጣ አልሳቀም ብሎ ነው የቀጣው። አንዱን ደግሞ ቡድኑ አቻ ወጥቶ ከሜዳ ሲወጣ እየሳቀ ነው ብሎ ለሊቱን ሙሉ ሲነዘንዘው ነበር። እኛ ደግሞ አስታራቂ ነበር።

“እኛ ከሰውዬው የወሰድነው ነገር አለ። ይህም ዲሲፕሊን ነው። ይሄንን አስቀምጦልናል። ሜዳም ውስጥ ከሜዳ ውጪም ተጫዋቾቹ የሚኖራቸውን ነገር አስቀምጦልናል። ዲሲፕሊን ሰፊ ቢሆንም ከፀጉር ጀምሮ ያስተካከለልን ሰው ነው። ይሄንን ተጫዋቾቹ አያቁትም። የፕሮፌሽናል ችግር አለ። ከዚህ በተጨማሪም የሥነ-ልቦና ችግር አለ። ምን ያህል ሥነ-ልቦናን የሚያነቃ እና የሚያስተምር ባለሙያ ሀገራችን አለ የሚለውም ሌላ ጥያቄ ነው።” በማለት ሀሳባቸውን ከገለፁ በኋላ ክራምፖቲች ከተጫዋቾቹ ጋር የነበራቸውን ዋነኛ ክፍተተ በተከታይነት አመላክተዋል።

“ዋናው ችግር የቋንቋ ችግር ነው። እንዴት ነው የምናስማማቸው? ከ23 ተጫዋቾች አራቱ ቋንቋ ከቻሉ ጥሩ ነው። ምክትል አሠልጣኞቹም ጋር የቋንቋ ውስንነት አለ። የሚያስተረጉሙት እነሱ ስለሆነ ሀሳቦች በጥሩ ሁኔታ መድረስ አለባቸው። ብዙ ነገሮች አየር ላይ ይቀራሉ።

“በአንድ ወቅት ተጫዋቾቹን ለማስተማር ሞከርን። በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ማታ ማታ እንዲማሩ አደረግን። ግን ከ15 ቀን በኋላ ተንጠባጥበው ጠፉ። በእኛ ቦታ ብትሆኑ የችግሩ ክብደት ይገባችኋል።” ካሉ በኋላ ከዚህ በኋላ የውጪ አሠልጣኝ አይመጣም? ለሚለው ጥያቄ “ተጫዋቾቹን ቋንቋ እናስተምራለን።” የሚል አጭር መልስ ሰጥተዋል።