ቅድመ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ሲዳማ ቡና

የስምንተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታን በሚከተለው ዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ከሽንፈት መልስ እርስ በእርስ የተገናኙት መከላከያ እና ሲዳማ ቡና ዳግም ከድል ጋር በመታረቅ ወደ አሸናፊነት ለመምጣት እና ደረጃቸውን ለማሻሻል ነገ ወሳኝ ፍልሚያ እንደሚያደርጉ ይገመታል።

በሰባት የሊጉ ጨዋታዎች አንድ ድል ብቻ ያደረገው ሲዳማ ቡና (በሁለተኛ ሳምንት ድሬዳዋን 3ለ0) ደከም ካለው ወቅታዊ ብቃቱ ለማገገም ነገ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በተለይ ሳይጠበቅ በሰባተኛ ሳምንት በፋሲል ከነማ ከደረሰበት አሸማቃቂ የአራት ለምንም ሽንፈት ለማገገም ከወትሮው በተለየ ጠንካራ አጨዋወት እንደሚያደርግ ይታመናል።

በፋሲሉ ጨዋታ ቡድኑ ለጥንቃቄ ቅድሚያ በመስጠት ለመጫወት ቢጥርም (በድህረ-ጨዋታ አስተያየት አሠልጣኙም አምነዋል) እጅግ የወረደ የመከላከል አደረጃጀት ሲከተል ስለነበረ ከጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጀምሮ ዋጋ ሲከፍል ነበር። ገና በአስራ ሰባት ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት ጎሎችን ያስተናገደበትን መንገድ ስናስታውስ ደግሞ በግል እና በቡድናዊ መዋቅር ሲሰሩ የነበሩ የመከላከል እፀፆች ጎልተው እንደነበር እናስታውሳለን። ታዲያ ገና በሰባት ጨዋታዎች ከጅማ በመቀጠል ከሰበታ ጋር በጣምራ የሊጉ ሁለተኛው ብዙ ግብ ያስተናገደ (ዘጠኝ) ክለብ የሆነው የአሠልጣኝ ገብረመድህን ስብስብም ብዙ የግብ ዕድሎችን በማይፈጥረው ነገርግን ስል በሆነው መከላከያ ነገም እንዳይቀጣ ትኩረት ሰጥቶ መግባት የግድ ይለዋል።

ቡድኑ በተረታበት ጨዋታ በመስመር ላይ የሚያደርጋቸው ጥቃቶች ቀንሰው ነበር። በተለይ በአንዳንድ ጨዋታዎች የቡድኑ የማጥቃት መነሻ ሲሆኑ የሚታዩት ሁለቱ መስመሮች ላይ የነበረው ክፍተት በጨዋታው ምላሽ እንዳይሰጥ አድርጎታል። በተለይ የቀኝ መስመር ተከላካዩ አማኑኤል ባለመኖሩ የመሐል ተከላካዩ ምንተስኖት እምብዛም ባለመደው ቦታ በመሰለፉ እና በግራ መስመር የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ቦታ አግኝቶ የነበረው እና ወደ ተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ እንዲገባ ፍቃድ የሚሰጠው ሰለሞን ደግሞ ገና ጨዋታው ግማሽ ሰዓት ሳይሞላ (በ22ኛው ደቂቃ) በጉዳት ተቀይሮ መውጣቱ ለወትሮ ጠንካራ የነበረውን ክፍል አሳስቶታል። ምናልባት ይህ ሽግግሮች የሚደረጉበት እና ተሻጋሪ ኳሶች የሚነሱበት ቦታም ነገ ተሻሽሎ ከቀረበ በጉዳት እና በቅጣት ዋነኛ ተመራጭ የመስመር ተከላካዮችን በነገው ጨዋታ ለማያሰልፉት መከላከያዎች ፈተና ነው።

በሰባቱ የሊጉ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ አቻ ወጥቶ በሦስቱ ተሸንፎ ቀሪዎቹን ሦስት ጨዋታዎች የረታው መከላከያ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ለተጋጣሚ (ቡና እና ሀዲያ) በድምሩ ስድስት ነጥብ ካስረከበ በኋላ ዳግም ወደ አሸናፊነት መመለሰን እያሰበ ድል ከራበው ሲዳማ ጋር ጠንካራ ጨዋታ ነገ ያከናውናል።

በሊጉ አንድም ጨዋታ ባላሸነፈው ሀዲያ ሆሳዕና የተረቱት መከላከያዎች በጨዋታው ሦስት ነጥብ ከመጣላቸው ባለፈ በእንቅስቃሴ ረገድ ብልጫ ተወስዶባቸው ታይቷል። በተለይ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከኳስ ውጪ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የተናበበ አለመሆኑ እና ለተጋጣሚ ተጫዋቾች ክፍተቶችን የሚቸር መሆኑ በስድስት የቀደሙት ጨዋታዎች ሁለት ጎሎችን ብቻ አስቆጥሮ የነበረው ሀዲያ በአንድ ጨዋታ ብቻ በስድስቱ ጨዋታዎች ያስቆጠራቸውን ጎሎች እንዲያገኝ ያደረገ ነበር። ይህ የመከላከል እንቅስቃሴ ደግሞ ነገ ወደ ቀደመ ጥንካሬው የማይመለስ ከሆነ ዳግም ችግር ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ቀድሞ መናገር ይቻላል።

መከላከያዎች ከጅማ በመቀጠል ሁለተኛ ትንሽ ግቦችን ያስቆጠሩ (ሰበታ፣ ሀዲያ እና አዳማ ጋር በጋራ) ቢሆንም አጋጣሚዎችን የመጨረስ ችግር እምብዛም አይታይባቸውም። በሀዲያው ጨዋታ ግን ሽግግሮቻቸው ዘለግ ያሉ ደቂቃዎችን የሚወስዱ እና የረጃጃም ኳሶቻቸው ስኬት የወረዱ መሆናቸው በሁለቱ አጋማሾች ለተቆጠረባቸው ጎል ፈጣን ምላሽ እንዳይሰጡ ያደረገ ይመስላል። አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌም በጨዋታው ከቀየሯቸው አራት የተጫዋች ቅያሪዎች በአስገዳጅ ሁኔታ በ25ኛው ደቂቃ ከወጣው ገናናው ረጋሳ ውጪ ሦስቱ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች መሆናቸውም ምን ያህል ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ ደካማ ጊዜ እንደነበረው የሚነግረን ነገር ነው። ይህ ከተሻሻለ ደግሞ ቡድኑ በጨዋታው አዎንታዊ ውጤት ይዞ እንዲወጣ የሚያደርግ ይመስላል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወሳኝ ተጫዋቾች ነገ አይኖሩም። በሲዳማ ቡና በኩል ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ሰለሞን ሀብቴ እና አማኑኤል እንዳለ በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን በመከላከያ በኩል ደግሞ ገናናው ረጋሳ፣ አዲሱ አቱላ፣ ኦኩቱ ኢማኑኤል እና ሰመረ ሀፍታይ በጉዳት ዳዊት ማሞ ደግሞ በቅጣት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

ዘጠኝ ሰዓት የሚጀምረውን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሠ እንደሚመሩትም ታውቋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ተጋጣሚዎቹ የሀያ ጨዋታ የሊግ ግንኙነት ሲኖራቸው ሲዳማ ቡና ሰባት መከላከያ ደግሞ ስድስት ጊዜ አሸናፊ ሆነዋል። ቀሪዎቹ ሰባት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ከተመዘገቡት 37 ግቦች ውስጥ 19ኙ የመከላከያ 18ቱ ደግሞ የሲዳማ ቡና ነበሩ።

ግምታዊ አሠላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

ተክለማርያም ሻንቆ

ምንተስኖት ከበደ – ጊት ጋትኩት- ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና

ቴዎድሮስ ታፈሰ – ሙሉዓለም መስፍን

ብሩክ ሙሉጌታ – ፍሬው ሰለሞን – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ይገዙ ቦጋለ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ልደቱ ጌታቸው – ኢብራሂም ሁሴን – አሌክስ ተሰማ – ዳዊት ወርቁ

ኢማኑኤል ላርዬ – ደሳለኝ ደባሽ

ኤርሚያስ ኃይሉ – ቢኒያም በላይ – ግሩም ሀጎስ

ገዛኸኝ ባልጉዳ