ሪፖርት | ሳቢ ያልነበረው የመከላከያ እና ሲዳማ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል

የስምንተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ በመከላከያ እና በሲዳማ መካከል ተደርጎ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

በሀዲያ ሆሳዕና ተረተው ለዛሬው ፍልሚያ የተዘጋጁት መከላከያዎች ሦስት ነጥብ ካስረከቡበት ጨዋታ ጉዳት ላይ የሚገኙት ገናናው ረጋሳን እና ኦኩቱ ኢማኑኤልን ጨምሮ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ የሆነው ዳዊት ማሞን በቢኒያም ላንቃሞ፣ ዳዊት ወርቁ እና አቤል ነጋሽ ሲተኩ በፋሲል ከነማ አራት ለምንም የተሸነፉት ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ግርማ በቀለን በጊት ጋትኩት፣ ብርሃኑ አሻሞን በዳዊት ተፈራ፣ ሰለሞን ሀብቴን በመሐሪ መና እንዲሁም ሀብታሙ ገዛኸኝን በቴዎድሮስ ታፈሰ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ጨዋታው ገና አምስት ደቂቃ ሳይሞላው የሲዳማ የግራ መስመር ተከላካይ መሐሪ መና በራሱ ሜዳ መሬቱ አንሸራቶት የተወውን ኳስ ብሩክ ሰሙ ፈጥኖ በማግኘት ወደ ግብነት እንዲቀየር ቢጥርም የመሐሪ የቡድን አጋሮች ስህተቱ ጎል እንዳይሆን አጋጣሚውን አምክነውታል። ሲዳማ ቡናዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሀሳብ ኖሯቸው ለመንቀሳቀስ ቢጥሩም ተደጋጋሚ የቅብብል ስህተቶችን እየፈፀሙ አደጋዎችን ሲጋብዙ ነበር። መከላከያዎች ደግሞ ከኳስ ውጪ አብዛኛውን ደቂቃ በማሳለፍ የሚያገኟቸውን ኳሶች በትንሽ ንክኪዎች ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመውሰድ ሲሞክሩ ነበር።

ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ የሚታይበት ጨዋታው 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያውን ወደ ግብ በቀጥታ የተመታ ሙከራ አስመልክቷል። በዚህም ሲዳማ ቡና በአጥቂው ይገዙ ቦጋለ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ በተመታ ኳስ ወደ ግብ ቀርቦ ነበር። ከደቂቃ በኋላም ይሁ አጥቂ ይገዙ ከቀኝ መስመር ምንተስኖት ከበደ ያሻገረውን ኳስ በሩቁ ቋሚ በመጠበቅ ግብ ለማድረግ ተንቀሳቅሶ ነበር። በ32ኛው ደቂቃ ደግሞ ጊት ጋትኩት አቤል ነጋሽ ላይ ጥፋት ሰርቶ የተገኘውን ራቅ ያለ የቅጣት ምት ቢኒያም በላይ ወደ ግብ በጥሩ ሁኔታ መትቶት የግብ ዘቡ ተክለማርያም ሻንቆ አምክኖበታል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቀ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ሲዳማዎች በራሳቸው በኩል የቅጣት ምት አግኝተው በዳዊት ተፈራ አማካኝነት ለማስቆጠር ጥረው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቶባቸዋል። መከላከያ ደግሞ የመሐል ተከላካዩ ያኩቡ መሐመድ የተሳሳተውን ኳስ በአቤል አማካኝነት ለመጠቀም ጥረው አጋማሹን እየመሩ የሚወጡበትን አጋጣሚ በድጋሜ ተክለማርያም አምክኖባቸዋል። አጋማሹም ያለ ግብ ዜሮ ለዜሮ ተጠናቋል።

የእንቅስቃሴ እድገት ያላሳየው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አሁንም በተመሳሳይ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ከማሳየት የተቆጠበ ነበር። በ63ኛው ደቂቃ ግን ከቅጣት ምት የተነሳን ኳስ ተከላካዮች ከገጩት በኋላ የደረሰው ይገዙ ኳሱን የአጋማሹ የመጀመሪያ ሙከራ አድርጎት ተመልሷል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ መከላከያ በራሱ በኩል እጅግ ለግብ የቀረበበትን አጋጣሚ ፈጥሮ ነበር። በዚህም ቢኒያም በላይ ከመሐል በቀኝ የውጪ እግሩ በተከላካዮች መሐከል ያሻገረውን ኳስ በ60ኛው ደቂቃ አቤል ነጋሽን ቀይሮ የገባው አኩዌር ቻሞ ለመጠቀም ሲጥር ጊት በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶበታል።

አሁንም በኳስ ቁጥጥር ብልጫቸው የቀጠሉት የአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ተጫዋቾች በ79ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት ለመሐሪ ቶሎ ሰጥተውት የሰላ ጥቃት ቢያደርጉም ክሌመንት ቦዬ በጥሩ ቅልጥፍና ወደ ውጪ አውጥቶባቸዋል። መከላከያዎች በበኩላቸው በራሳቸው ሜዳ ላይ መቆየትን መርጠው አልፎ አልፎ ብቻ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል እየደረሱ ጥቃት ለመሰንዘር ቢጥሩም ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። ሲዳማዎች ግን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ኖሯቸው ቢጫወቱም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻሉም። በ93ኛው ደቂቃ ግን ከግራ መስመር ይገዙ ይዞት የገባውን ኳስ ለጥቂት ግብ ሊያደርጉት ነበር። ጨዋታው ግብ ሳያስተናግድ በአቻ ውጤት ተደምድሟል።

በውጤቱ መሠረት መከላከያ ነጥቡን 11 በማድረስ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሲዳማ ቡናም ያለው ሰባት ነጥብ ላይ አንድ አክሎ አንድ ደረጃ በማሻሻል 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።