ሪፖርት | ጥሩ ፉክክር የታየበት የምሽቱ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

በባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ መካከል የተከናወነው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በአዝናኝነት ቢዘልቅም 0-0 ተቋጭቷል።

የመጨረሻ ጨዋታቸውን በድል የተወጡት የዛሬዎቹ ተጋጣሚዎች በየፊናቸው ሁለት ለውጦች አድርገዋል። ባህር ዳር ከተማ በፈቱዲን ጀማል እና በረከት ጥጋቡ ምትክ ሰለሞን ወዴሳ እና መሳይ አገኘሁን ሲጠቀም ፋሲል ከነማም ከድር ኩሊባሊ እና በዛብህ መለዮን በአቻለው ታመነ እና ሳሙኤል ዮሐንስ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል።

ፈጣን ጅማሮ በነበረው ጨዋታ ፋሲል ከነማዎች ተጋጣሚያቸው ወደ ራሱ ሜዳ እንዲሳብ ያደረገ ጫና ፈጥረዋል። 4ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ ከበረከት ደስታ የደረሰውን ኳስ በግንባሩ ጨርፎ በማመቻቸት ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራም በፋሲል ገብረሚካኤል ጥረት ዳነ እንጂ ቡድኑ በቶሎ ለመምራት ተቃርቦ ነበር። ባህር ዳሮች የተፈጠረባቸውን ጫና ቀስ ብለው በማርገብ ወደ ጨዋታው ምት ሲመለሱ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ግብ ለመድረስ ጥረዋል። ከፋሲል ተከላካዮች ጀርባ ቀጥተኝነትን በቀላቀለ መልኩ ለመግባት ያደረጉት የነበረው ጥረት ግን ከጨዋታ ውጪ በሆኑ አቋቋሞች በተደጋጋሚ ይቋረጥ ነበር።


በቀጣይ ደቂቃዎች በመሀል ላይ ፍልሚያዎች ተገድቦ የቆየው ጨዋታ ቀስ በቀስ ሌሎች ሙከራዎችን አሳይቶናል።19ኛው ደቂቃ ላይ የያሬድ ባየህ የመሀል ሜዳ ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ሲደርስ በሽመክት ጉግሳ ተጨርፎ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። ባህር ዳሮችም ወዲያው በፈጣን ጥቃት ፋሲል ሳጥን መግቢያ ላይ ደርሰው ማዉሊ ያደረገው ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። ጨዋታው ግጭቶች እየበረከቱበት ሲቀጥልም 26ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲሎች ከርቀት ያገኙትን ቅጣት ምት ኦኪኪ መትቶ ግብጠባቂው ፋሲል ጨርፎት የግቡ ቋሚ መልሶታል።


ከውሀ ዕረፍቱም በኋላ ለዓይን ሳቢ ፉክክር እያስመለከተን በቀጠለው ጨዋታ የተሻለ የኳስ ቀጥጥርን የያዙት ፋሲሎች በተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ክፍተቶችን በመፈለግ ቆይተዋል። የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም በመሞከር ውስጥ ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ የሚልኳቸው ኳሶችም ይታዩ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ 33ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ ከዓለምብርሀን ይግዛው የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ይጠቀሳል። ።

ከኋላ አምስት ሆነው ቀዳዶችን ለመድፈን እና አደጋዎችን ለማራቅ ያደረጉት ጥረት በስኬት የቀጠለላቸው ባህር ዳሮችም በቀጥተኛ ኳሶች የዓሊ ሱለይማንን ፍጥነት ለመጠቀም ሲሞክሩ ይታይ ነበር። ሆኖም የቡድኑን የማጥቃት ሽግግር ሲያሳልጥ የነበረው የፍፁም ዓለሙ እና የማውሊ ጥምረት በተሳካ ሁኔታ የፈጠረው ቅብብል 43ኛው ደቂቃ ላይ ነበር የመልሶ ማጥቃት ውጥኑ የሰመረለት። በዚህ መልክ ከማዉሊ እግር ሳጥን ውስጥ የደረሰውን ኳስ አብዱልከሪም ኒኪማ በቀኝ አምልጦ በመግባት ያደረገው አደገኛ ሙከራ ለጥቂት በጎን የወጣ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ባህርዳሮች የመስመር ተመላላሾቻቸውን ወደ ፊት ገፍተው ኳስ በሦስቱ ተከላካዮች ከኋላ የመመስረት ምልክት አሳይተው ነበር። በእንቅስቃሴ የግብ ዕድል ባይፈጥሩም 48ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ ያደረገው የቅጣት ምት ሙከራ በሳማኪ ቡጢ ተመልሷል። ይህ አጀማመራቸው ግን በተለይ ኦሴይ ማዉሊ በጉዳት በበረከት ጥጋቡ ከተቀየረ በኋላ ለዘብ ብሏል። ይልቁኑም ፋሲሎች የማጥቃት ብርታታቸውን መልሰው ሲያገኙ ከቀኝ መስመር የሚነሱ ኳሶቻቸውም በድጋሚ መታየት ጀምረዋል። ይሁን እንዳሻውን በሱራፌል ዳኛቸው የቀየሩበት ቅፅበትም ቡድኑ ያለተፈጥሯዊ ተከላካይ አማካይ ፈጣሪ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾችን በማብዛት ይበልጥ አጥቅቶ ለመጫወት መቁረጡን ያሳየ ነበር።

ያም ሆኖ የባህር ዳር የመከላከል አደረጃጀት ክፍተት ሳይሰጥ ቆይቷል። ፋሲሎች ዘግይተው ወደ ግብ በደረሱበት ቅፅበት በረከት ደስታ 74ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ ውስጥ ያደረሰው ኳስ ጥሩ የግብ ዕድል ቢወጥቷል። በናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ተሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቷል። ፋሲሎች የተከፈተውን የተከላካይ አማካይ ቦታቸውን በመስመር ተከላካዮቻቸው ወደ መሀል የሚጠቡ ሩጫዎች ለመሸፈን ሲጥሩ ባህርዳሮች በተለይ በተከፈተው የግራ መስመር አድልተው ፈጣን ጥቃት ለመሰንዘር ይጥሩ ነበር።

ከጅምሩ ንክኪዎች የበረከቱበት ጨዋታ በመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ ይገኝ የነበረው አህመድ ረሺድ 81ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ደስታ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ይህ እንቅስቃሴ በቅጣት ምት ሲቀጥል ሱራፌል ሲያሻማ ኩሊባሊ ነፃ ሆኖ በግንባሩ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ነበር ወደ ውጪ የወጣው። ፋሲሎች ፍቃዱ ዓለሙን ጨምረው በማስገባት የባህር ዳርን የተጫዋች ጉድለት ለመጥቀም ጥረዋል። በድጋሚ የባህርዳሮች የአቋቃም ችግር በታየበት የሱራፌል ዳኛቸው 86ኛ ደቂቃ ቅጣት ምት ዓለምብርሀን ነፃ ሆኖ ያገኘውን የግንባር ኳስ ግን አምክኗል። የመጨረሻው የጨዋታው ቅፅበቶች በግለቱ ቀጥሎ ተደጋጋሚ ጉሽሚያዎችን እያሳየን ወደ ፍፃሜው ቀርቧል። በጭማሪ ደቂቃዎች ፋሲል ከነማዎች ተቀይሮ በገባው አቤል እያዩ የሳጥን ውጪ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን ባህር ዳሮች አዳጋ ፈጣሪ ኳሶሾችን ከግብ ክልላቸው ማራቅ ላይ አተኩረዋል። ጨዋታው ሰከንዶች ሲቀሩት ግን ዓሊ ሱለይማን በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ከሳጥን ውስጥ ግብ ለማድረግ ሞክሮ ወደ ውጪ ወጥቶበት ማራኪ የነበረው ፍልሚያም ያለግብ ተጠናቋል።

በውጤቱ ፋሲል ከነማ ወደ 15 ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ወደ 14 ነጥባቸው ሲያድጉ በነበሩበት አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።