ቅድመ ዳሰሳ | አዲስ አበባ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በሳምንቱን ሁለተኛ የጨዋታ ዕለት የምሽት መርሐ ግብር ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በሊጉ ሰንጠሩዥ ከአጋማሽ በታች የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ዕኩል አስር ነጥቦችን ይዘዋል። ይሁን እንጂ የሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎቻቸው ውጤት የተለያየ እንድምታ ነበራቸው። ሀዋሳ ከተማ ከድል ርቆ ከሰነበተባቸው ሦስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ ሲያሳካ አዲስ አበባ ከተማ በተቃራኒው ከአራት ጨዋታዎች አስር ነጥቦችን ወደ ኪሱ ቢያስገባም ወደ ሽንፈት የተመለሰበት ነበር። ይህ መሆኑም ነገ ሀዋሳ መልሶ ያገኘውን አሸናፊነት ለማስቀጠል አዲስ አበባ ደግሞ ወደ ተከታታይ ሽንፈቶች ላለመሄድ ጥረት የሚያደርጉበት ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በሊጉ የቡድኖች የሜዳ ላይ የተነሳሽነት ደረጃ ከሳምንት ሳምንት ሲለያይ ይስተዋላል። ያም ሆኖ የነገ ተጋጣሚዎቹ ከውጤት ብቻም ሳይሆን ከቡድን መንፈስ አንፃር የመጨረሻ ግጥሚያዎቻቸው ምልክት ሰጪ ነበሩ። ከአሰልጣኝ ኢስማኤል አበበከር ስንብት በኋላ በአስልጣኝ ደምሰው ፍቃዱ ስር የአሰልጣኞችን ሹም ሽርን ተከትሎ የሚመጣ መነሳሳት ታይቶበት የነበረው አዲስ አበባ በወልቂጤው ጨዋታ ቀዝቀዝ ብሎ ተመልክተነዋል። ይህም ‘የቡድኑ አለቃ የጫጉላ ጊዜ አብቅቶ ይሆን ?’ የሚል ጥያቄ ሲያስነሳ ነገ ስብስቡ ሜዳ ላይ የሚኖረው መንፈስ የዚህን ግምት አቅጣጫ የሚወስን ይመስላል። በሀዋሳ ከተማ በኩል ግን የሰበታው ድል ከውጤቱ ባሻገር ከመመራት ተነስቶ በተደረገ ጥረት የተገኘ እንደመሆኑ ቡድኑ በተሻለ የሥነ ልቦና ደረጃ ወደ ሜዳ እንዲገባ መሰረት የሚሆነው ይመስላል።

ሌላው የትኩረት ነጥብ የሚሆነው ሁለቱም ተጋጣሚዎች ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ለፈጣን ጥቃት ቅድሚያ የሚሰጡ የመሆናቸው ጉዳይ ነው። በዚህ ረገድ በተለይ ግብ ካገኙ በኋላ ጠጠር ብለው በመከላከል ወደ መስመሮች ያደሉ ጥቃቶችን መፈፀም የሚቀናቸው አዲስ አበባዎች በወልቂጤው ጨዋታ ተጋጣሚ የኳስ ቁጥጥሩን ሲለቅላቸው በሚያስፈልገው ልክ ሰብረው መግባት ሲቸገሩ መታየታቸው ትኩረትን ይስባል። ከዚህ አንፃር እና ተከታታይ ሽንፈትን ለማስወገድ ከሚኖራቸው ሀሳብ አንፃር ከጅምሩ የነገ ተጋጣሚያቸውን ወደሜዳቸው በመጋበዝ ከተከላካይ መስመሩ ጀርባ ለመግባት ቅድሚያ ሊሰጡ እንደሚችሉ ይታመናል። በዚህ አኳኋንም ግን የመጨረሻ ዕድሎችን ሲያባክኑ የተመለክትንበትን መንገድ አሻሽለው መቅረብ ሌላኛው የቤት ሥራቸው ይሆናል።

ለሀዋሳ ከተማ የነገ የማጥቃት ሂደት ትልቁ የምስራች ሙሉ ዕምነት የሚጣልባቸው ሦስቱ የፊት አጥቂዎች ወደ ግብ አስቆጣሪናታቸው በተመለሱ ማግስት የሚያደርጉት ጨዋታ መሆኑ ነው። እዚህ ላይ ግን ከተከላካይ ጀርባ ሰፊ ክፍተት ሲያገኙ አስፈሪነታቸው የሚጎላው አጥቂዎቹ በጥልቀት ሊያፈገፍግ ከሚችለው የአዲስ አበባ ከተማን መከላከል በምን መንገድ ማስከፈት ይችላሉ የሚለው ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። በእርግጥ አዲስ አበቤዎቹ በወልቂጤው ጨዋታ የታየባቸው የመናበብ እና የጊዜ አጠባበቅ ችግር ካልታረመ ለሀዋሳ የፊት መስመር ገፀ በረከት የሚሆንበት ዕድል አይጠፋም። ከዚህ በተጨማሪ በድንቅ አቋም ላይ ይገኝ የነበረው ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ አለመሰለፍም ለአዲስ አበባ የኋላ ክፍል ተጨማሪ ስጋት መፍጠሩ አይቀረም።

የነገውን ተጋጣሚዎች የቡድን ዜና ስንመለከት ሀዋሳ ከተማ ፀጋአብ ዮሐንስ እና አብዱልባሲጥ ከማልን በጉዳት ፀጋሰው ድማሙን ደግሞ በቅጣት ምክንያት ያጣል። በአዲስ አበባ በኩል ደግሞ የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት ቴዎድሮስ ሀሙ ፣ ፈይሰል ሙዘሚል እና ነብዩ ዱላ በተጨማሪ ሮቤል ግርማ በህመም ዳንኤል ተሾመ ደግሞ በብብሽሽት ጉዳት በነገው ጨዋታ እንደሚይኖሩ ሰምተናል።

ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ አባይነህ ሙላት በመሀል ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– አዲስ አበባ ከተማ በታሪኩ የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን ያደረገው ከሀዋሳ ጋር በ2009 ሲሆን በወቅቱ ሀዋሳ ላይ 2-0 አሸንፎ ነበር። በሁለተኛ ዙር ደግሞ ሀዋሳ 1-0 አሸንፏል። የቡድኖቹ የግንኙነት ታሪክም በሁለቱ ጨዋታዎች የተገደበ ነው።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ወንድወሰን ገረመው

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ልመንህ ታደሰ – ሳሙኤል አስፈሪ – ያሬድ ሀሰን

ኤልያስ አህመድ – ቻርለስ ሪባኑ – ሙለቀን አዲሱ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ አዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን

ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)

መሐመድ ሙንታሪ

ዳንኤል ደርቤ – ላውረንስ ላርቴ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ዮሐንስ ሱጌቦ

ወንድማገኝ ኃይሉ – ዳዊት ታደሰ – በቃሉ ገነነ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ