የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሰፊ ውጤት አሸንፎ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል

በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች የአለም ዋንጫ ማጣርያ ሦስተኛ ዙር የቦትስዋና አቻውን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን 8-2 በሆነ የድምር ውጤት በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ቦትስዋና ላይ 3-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የተመለሰው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፍፁም የበላይነት በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለጊዜ በቦትስዋና የሜዳ ክፍል አጋድሎ የተካሄደ ነበር።  ገና ከጅምሩ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት የኢትዮጵያ ከ20 በታች ብሔራዊ ቡድን በተለይ በ13ኛው ደቂቃ ኘቦኘ የን ከመስመር ያቀበለቻትን ኳስ ተጠቅማ ቱሪስት ለማ ያመከነችው ግልፅ ኳስ እንዲሁም በ16ኛው ደቂቃ አርአያት አዶንጎ ከመስመር ገብታ ወደ ግብ ሞክራ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጡባቸው ኳሶች እጅግ አስቆጭ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ከእንቅስቃሴው መነሻነት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ማስቆጠሩ ነገር የሚቀር ባልመሰለበት ሁኔታ የቡድኑ ግብ ፍለጋ የዘለቀው ለ26 ያክል ደቂቃዎች ነበር ፤ በዚህ ደቂቃ አምበሏ ናርዶስ ጌትነት ከቀኝ መስመር ወደ ውስጥ ያሻማችውን ኳስ ለመከላከል ጥረት ያደረገችው የቦትስዋናዋ ክሪስቲያና ሞኒያትሲ የገጨችው ኳስ አቅጣጫውን ስቶ በራሷ መረብ ላይ ማረፉን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆን የቻለች ሲሆን በዚህ ግብ የተነቃቁ የሚመስሉት የአሰልጣኝ ፍሬው ልጆች አከታትለው ሶስት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

በ28ኛው ደቂቃ አርያት አዶንግ ከግራ መስመር በግል ጥረት አጥብባ የገባችውን ኳስ በቀጥታ ስታስቆጥር ከአራት ደቂቃዎች በኃላ ደግሞ ረድኤት አስረሳኸኝ የጨዋታውን ምርጥ ግብ ከርቀት አክርራ በመምታት ከመረብ ስታዋሃድ በ35ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረላትን ኳስ ሳጥን ውስጥ በጥሩ አቋቋም የነበረችው ረድኤት አስረሳኸኝ ተቆጣጥራ በድጋሚ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ኢትዮጵያ 4-0 መሪ ማድረግ ችለዋል።

በአጋማሹ ደካማ የነበሩት ቦትስዋናዎች በአጋማሹ ሳይጠበቁ በ39ኛው ደቂቃ ሺግፋትሶ ኖምሳ ሞሶትሆ ካደረገችው እና በአግዳሚው ከተመለሰባት አስደንጋጭ ሙከራ ውጭ እንደ ቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ እጅግ ደካማ እንቅስቃሴን አሳይተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ከመጀመሪያው አንፃር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደ መጀመሪያው ሁሉ በማጥቃት ጨዋታውን የጀመረበት ነበር።

በጨዋታው ፍፁም የበላይ የነበሩት ኢትዮጵያዎች በ58ኛው ደቂቃ አምስተኛ ግብ አክለዋል ፤ በቦትስዋና ግብጠባቂ ስህተት የተገኘውን ኳስ ቱሪስት ለማ ከግቡ ትይዩ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ወደ መሀል ያሻማችውን ኳስ የቦትስዋናዋ ሎሮትዋ ሞቶሎግኤልዋ በራሷ መረብ ላይ አስቆጥራለች።

በቀሩት የአጋማሹ ደቂቃዎች ኢትዮጵያዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ አጋማሽ መድረስ ቢችሉም የጎል ሙከራዎችን ግን ለመፍጠር ተቸግረው ተስተውሏል ፤ ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባቸው አረጋሽ ካልሳ በግል ጥረት ሁለት አጋጣሚዎችን ብትፈጥርም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ተጫዋቾች መቀዛቀዝን ተከትሎ በመጠኑም ቢሆን የተነቃቁት ቦትስዋናዎች በ87ኛው ደቂቃ ሺግፋትሶ ኖምሳ ሞሶትሆ ከሳጥን ውጭ አክርራ በመምታት ባስቆጠረችው ግብ በባዶ ከመሸነፍ ድነዋል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በአራተኛ ዙር ማጣርያ የታንዛንያ እና ቡሩንዲ አሸናፊን የሚገጥም ይሆናል።