የአሰልጣኞች አስተያየት | ወልቂጤ ከተማ 0-1 ኢትዮጵያ ቡና

በዊሊያም ሰለሞን ግብ ኢትዮጵያ ቡና ወልቂጤ ከተማን ከረታበት ጨዋታ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ከስፐር ስፖርት ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለጨዋታው

ጥሩ ነበር ።ባለፈው ጨዋታ በተወሰነ ደረጃ አርመነው የነበረው ዛሬ ደግሞ በተመሳሳይ የታየው ችግር ከጅማ እና ከመከላከያ ጋር ስንጫወት ጎል ካገባን በኋላ የታየው ነው። ሁል ጊዜ ጎል ካገባህ በኋላ ተጋጣሚ ጫናውን ይጨምራል። ያኔ እኛ የምንሰጠው ምላሽ ከመጀመሪያው ያደገ መሆን አለበት። እዛ ነገር ላይ ትንሽ ንቃት ያስፈልገናል። ሌላው ተጋጣሚ ተጫዋች ሲወጣበት የተከፈተ ቦታ እንዳገኘህ ነው የምታስበው እና የመጀመሪያ ነገርህን ትለቃለህ እሱን ነው ማስተካከል ያለብን። ሰው ወጥቶባቸዋል የቁጥር ክፍተት አለ። ግን የተከፈተ ቦታ እንዳገኘ ሰው ዝም ብላችሁ ወደፊት እንዳትሄዱ በትክክል ጨዋታውን እንያዝ የሚል ሀሳብ ነበረኝ። ግን ጥድፊያ ነበር። በእርግጥ የተከፈቱ ቦታዎች ነበሩ። ነገር ግን እነዛ መልሰው ያስጠቁሀል። ሰው ከወጣባቸው በኋላ እኛ ጋር ጥድፊያ ነበር ፤ ጨዋታ ያለመቆጣጠር ነገር። በውጤት ዳረጃ ግን ጥሩ ነው።

ከኳስ ቁጥጥራቸው አንፃር በቂ ዕድል ስላለመፍጠራቸው

ሁል ጊዜ የሚቀጥል ነገር ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ። እነሱ መጀመሪያ ላይ ሁለት ሰው ከፊት አድርገው ነበር የሚጫወቱት። ከኋላ ስምንት ሰው አድርገው ነው የሚጫወቱት ከግብ ጠባቂው ውጪ ማለት ነው። እስራኤል እና ጌታነህ ዲያጎናል እየሰሩ እንደገና አንዱ ሰው እየተመለሰ መሀል ያሉትን ይረዳል። ቁጥራቸው ብዙ ነው ፣ እንደፈለከው የመጫወቻ ቦታ አታገኝም ፤ የሜዳውም ጉዳይ አብሮ አለ። ስለዚህ በቀላሉ የተከፈቱ ቦታዎችን እያገኙ መሞከር አስቸጋሪ ነው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ። ለዛ ነው ብዬ ነው የማስበው ፤ እንደብልጫው ብዙ ማግባት ያተቻለው።

ስለመንግሥቱ ወርቁ ትውስታ

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ መሰረት ከጣሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ ነው። እኔንም በአዲስ አበባ ምርጥ ውስጥ በተጫዋችነት አሰልጥኖኛል የተወሰነ ጊዜ። ረጅም ጊዜ ያሰለጠናቸው የቅርብ ጓደኞቼም አሉ። ስላለው ብቃት ስላለው ችሎታ ፣ ለረጅም ጊዜ ወጥ ይሆነ ነገር ይፈልግ የነበረ ሰው ነው። ዝም ብሎ ጊዜያዊ ድል ይፈልግ የነበረ ሰው አይደለም። በተጫዋችነቱም በአሰልጣኝነቱም ለኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቅ ነገር ያበረከተ ሰው ነው።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – ወልቂጤ ከተማ

ስለጨዋታው

በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ከፍተኛ የማጥቃት ብልጫ ነበረን። በዛ ሰዓት ጎል ማግባት ነበረብን ብዬ እገምታለሁ። ዛሬ ኳስ የሚይዝ ቡድን ጋር ነው የተጫወትነው ግን የተመለከታችሁት ነገር ግን የተገላቢጦሽ ነበር። በጣም አጥቅተን ተጫውተናል ፤ ግብ ጠባቂያችን በቀይ ካርድ እስኪወጣ ድረስ። በቡድኔ ላይ ተስፋ ሰጪ ነገር ስላየሁ ብዙም አልተከፋሁም።

ስለፊት አጥቂዎቹ ጥምረት

ለእስራኤል እና ለጌታነህ የሰጠኋቸውን ኃላፊነት በትልክክል ተወጥተዋል። ኳሱ መረብ ላይ አይረፍ እንጂ የነበራቸው እንቅስቃሴ ካሳየኋቸው ጋር ጥሩ ሆኖ ያየሁባቸው ስለሆነ ወደፊት ጎል የማስቆጠሩን ነገር በትክክል እንደምንቀርፈው አይቻለሁ። ሁለቱም ላይ ጥሩ ነገሮች አይቻለሁ። ውጪም ብዙ አጥቂዎች አሉኝ። እነሱም ላይ ጥሩ ስራ ሰርተን ወደማሸነፉ እንመጣለን።

በድኑ ግብ እያስቆጠረ ስላለመሆኑ

ጨዋታው ውጥረት ነበረው። ቡድኖች ያገቡትን ኳስ አስጠብቀው ለመውጣት ነው የሚጫወቱት። ዛሬ ሰው ወጥቶብን እንኳን ኢትዮጵያ ቡና ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ነው የተጫወተው። እና ስመለከተው አሰልጣኞች ላይ ጭንቀትም አለ። እኔ ነፃ ሆኜ ነው የምሰራው በሌሎች ቡድኖች ላይ ግን የተመለከትኩት ነገር ይህንን ነው። አሰልጣኞች ሲረጋጉ ወደፊት ይህ ነገር ይቀረፋል የሚል ዕምነት አለኝ።

ስለሲልቪያን ግቦሆ ቀይ ካርድ

ተገቢ አይድለም። ዳኛ የራሱ ውሳኔ ሊኖረው ይችላል ፤ እኔ ስለዳኛ መናገር አልፈልግም። እኛ እንደምንሳሳተው እነሱም ሊሳሳቱ ይችላሉ። ስህተቱ ሲበዛ ነው መጥፎ። በአጠቃላይ እሱ የወጣበት ትልቅ ስህተት ነው። አንድ ፕሮፌሽናል ተጫዋች ይህንን ማድረግ የለበትም ስለዚህ መታረም አለበት ብዬ እገምታለሁ። በዲስፕሊን ጉዳይ አልደራደርም።