ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ሰበታ ከተማ

ከድል ጋር ለመታረቅ የሚደረገውን የሳምንቱን የመጨረሻ ጨዋታ በዳሰሳችን ተመልክተነዋል።

ጅማ እና ሰበታ እስካሁን ድረስ በሊጉ ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ ሳይችሉ ነገ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ጅማ አባ ጅፋሮች ከሽንፈት ተላቀው የመጀመሪያ ነጥባቸውን ያገኙት ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ነበር። በአንድ ደረጃ ብቻ ከፍ የሚለው ሰበታ ከተማም ቢሆን እስካሁን ከሦስት አቻዎች የዘለለ ውጤት ሊያስመግብ አልቻለም። ከዚህ አንፃር የነገው ጨዋታ በአቻ ውጤት እስካልተጠናቀቀ ድረስ አንዳቸውን ካሉበት የተዳከመ የስነ ልቦና ደረጃ ለማንቃት ያለው አስተዋፅዖ በምንም የሚተካ አይመስልም።

ከውጤት ባሻገር ኳስ መስርተው ለመጫወት ሲጥሩ የሚታዩት ሁለቱ ቡድኖች ተመሳሳይ ችግሮች ይታዩባቸዋል። ከዚህ ውስጥ አንዱ ወጥ የሆኑ እና በድግግሞሽ የተላመዱ ቀዳሚ ተሰላፊዎችን የመለየት ችግር አንዱ ነው። በዚህ ረገድ የውጤት ማጣቱ ሰውን በሰው በመተካት ነገሮችን ለማስተካከል እንዲሞክሩ ያደረጋቸው ይመስላል። ከአሰላለፍ ምርጫ ደግሞ አንፃር ሰበታ ከተማ የተሻለ ወጥነት የሚታይበት ሲሆን በየጊዜው የተለያየ ቅርፅ ይዞ የሚመጣው ጅማ አባ ጅፋር ግን የማይጨበጥ ሆኗል። ከእነዚህ ችግሮች ጋር የተያያዘ በሚመስል መልኩም ቡድኖቹ ለመከተል በሚፈልጉት አጨዋወት ውስጥ ገፍተው ወደ ተጋጣሚ ሜዳ የሚገቡባቸው አጋጣሚዎች ውስን ሲሆኑ ይታያል።

ይህ ችግር እንዳለ ሆኖ ጅማ በባህር ዳሩ እና በአርባምንጩ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ መሻሻሎች ታይተውበታል። ይህን ጅምሩን ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ይበልጥ እርጋታን እና ስክነትን ጨምሮ ማሻሻል ይጠበቅበታል። የፊት መስመር ተሰላፊዎቹን በራስ መተማመን መልሶ ለማግኘትም ግቦች እጅግ አስፈላጊ በመሆናቸው የማጥቃት ፍሰቱን ፍጥነት ከፍ አድርጎ የግብ ዕድሎችን ጥራት እና ቁጥር መጨመር አስፈላጊው ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ሳያስተናግድ በወጣበት የአርባምንጩ ጨዋታ ላይ የወጣቶቹ አላዛር ማርቆስ እና የአብስራ ተስፋዬን የግል ብቃት ከማስጠበቅ በተጨማሪ ግብ በማግባት ፍላጎት ውስጥ ለፈጣን ሽግግሮች የሚለጥባቸው ቅፅበቶች በቶሎ ማደራጀት መቻልም በነገው ጨዋታ የሚያስፈልገው ሌላኛው ማስተካከያ ነው።

ሰበታ ከተማ እንደተጋጣሚው ሁሉ ሽንቁሮቹ ብዙ ቢሆኑም የጠንካራ ጎኖቹ ወዲያው ወደ ድክመት መለወጥ ከሁሉም በላይ ስጋት ይሆንበታል። በሁለት ጨዋታዎች መረቡን ያለማስደፈር ሂደት የነበረው ቡድኑ በሀዋሳው ጨዋታ ያሳየው ግለሰባዊ እና ቡድናዊ ስህተቶች በዚህ መንገድ የሚገለጡ ናቸው። በዱሬሳ ሹቢሳ መመለስ የተነቃቃው የቡድኑ የማጥቃት ሂደትም ሙሉ ዕምነት የሚጥልበት የጨዋታ አቀጣጣይ አሁንም አለማግኘቱ በወጥነት ጫና ፈጥሮ እንዳይጫወት እያደረገደው ይገኛል። በነገው ጨዋታ ያሉበት የቅጣት እና ጉዳት ዜናዎች መበራከት ሲታሰብ ደግሞ ደካማ ጎኖቹን አሻሽሎ የመምጣት ፈተናውን ከፍ የሚያደርግበት ይመስላል።

በጨዋታው ጅማ አባ ጅፋር አሳሪ አልመሀዲን በጉዳት ያጣል። በሰበታ በኩል ከበረከት ሳሙኤል ቅጣት ሌላ የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙትን መሀመድ አበራ እና አክሊሉ ዋለልኝ በተጨማሪ አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ፣ ታፈሰ ሰርካ ፣ ዮናስ አቡሌ እና ጌቱ ወልደአማኑኤል የጉዳት ዝርዝሩን ተቀላቅለዋል፡፡ የአራት ወራት ቆይታ የነበረው ናሚቢያዊው አጥቂ ጂኒያስ ናንጄቤ ደግሞ በስምምነት ከክለቡ ጋር ተለያይቷል።

ጨዋታው በፌደራል ዳኛ ሀብታሙ መንግሥቴ የመሀል ዳኝነት ይከናወናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– አምና በሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ በቅድሚያ 1-1 ተለያይተው በሁለተኛው ዙር ጨዋታ ሰበታ ከተማ 2-1 ማሸነፍ ችሏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-2-3-1)

አላዛር ማርቆስ

በላይ አባይነህ – ተስፋዬ መላኩ – የአብስራ ሙሉጌታ – ወንድምአገኝ ማርቆስ

ሙሴ ካበላ – መስዑድ መሀመድ

ዱላ ሙላቱ – ምስጋናው መላኩ – መሀመድኑር ናስር

ዳዊት ፍቃዱ

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ለዓለም ብርሀኑ

ጌቱ ኃይለማሪያም – ቢያድግልኝ ኤሊያስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

አንተነህ ናደው – በኃይሉ ግርማ

ሳሙኤል ሳሊሶ – ዘላለም ኢሳይያስ – ዱሬሳ ሹቢሳ

ፍፁም ገብረማርያም