ሀድያ ሆሳዕና እና ድሬዳዋ ከተማን የመራው ዳኛ ቅጣት ተላለፈበት

በስምንተኛው ሳምንት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀድያ ሆሳዕና ድሬዳዋ ከተማን 3-2 ሲያሸንፍ ጨዋታውን መርተው በነበሩት የዕለቱ ዋና ዳኛ ላይ የስንብት ውሳኔ ሲተላለፍ ለአንድ ዳኛ ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል፡፡

የ2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እየተደረጉ ስምንተኛ ሳምንት ላይ ደርሰዋል፡፡ የዘንድሮው የሊጉ ውድድር ጠንካራ ፉክክር እየታየበት የሚገኝ ሲሆን በውድድሩ ላይ እየታዩ የሚገኙ የዳኞች ውሳኔዎችም አነጋጋሪ ሆነው ቀጥለዋል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከተካሄዱ ጨዋታዎች መካከል ሀድያ ሆሳዕና ከመመራት ተነስቶ ድሬዳዋ ከተማን 3-2 መርታት ሲችል ጨዋታውን መርተው የነበሩት ፌድራል ዋና ዳኛ ዓለማየሁ ለገሰ በጨወታው ሦስት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል። በተለይ በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ደቂቃዎች የሀድያ ሆሳዕናው ተከላካይ ፍሬዘር ካሳ በአብዱለጢፍ መሀመድ ላይ ከሳጥን ውጪ በሰራው ጥፋት የዕለቱ አልቢትር የፍፁም ቅጣት ምት መስጠታቸው ትኩረት የሚስብ ነበር። በዚህ መነሻነት ከሳጥን ውጪ የተሰራ ጥፋትን ፍፁም ቅጣት ምት ብለው በመስጠታቸው ቀጣይ የሊጉን ጨዋታዎች እንዳይመሩ ተወስኖባቸዋል፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ የጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማን ከባህር ዳር ከተማ ያገናኘውን ጨዋታ የመሩት ፌደራል ዳኛ ቢኒያም ወርቃገኘሁ ለፋሲሉ የመስመር አጥቂ በረከት ደስታ ሁለት ቢጫ የሰጡ የሚመስል አካላዊ እንቅስቃሴን በማሳየታቸው በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ውድድሩን እንዲያጠናቅቁ ተደርጓል፡፡

ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥፋቶችን ሲፈፅሙ የነበሩ እንደ ምስጋናው መላኩ እና ብርሀኑ መኩሪያ ዓይነት ዋና ዳኞች ላይ ቅጣት መጣሉ የሚታወስ ቢሆንም ኢንተርናሽናል ዳኛ ሆነው ጥፋት ሲፈፅሙ የሚታዩ ዳኞች ላይ ቅጣት ያለመጣሉ ጉዳይ በበርካቶች ጥያቄ እያስነሳ የሚገኝ ጉዳይ እየሆነ መጥቷል፡፡