ከፍተኛ ሊግ | የ14ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የከፍተኛ ሊግ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ሲጀምሩ የምድብ አንድ መሪዎቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቤንች ማጂ ቡና ሲያሸንፉ የምድብ ሁለት እና ሦስት መሪዎች ነጥብ ጥለዋል።

በዳንኤል መስፍን ፣ ቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ

የጠዋት ጨዋታዎች

ቤንች ማጂ ቡና ከ ጋሞ ጨንቻ – ምድብ \’ሀ\’

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ የሁለተኛው ዙር ውድድር በአሰላ አረንጓዴ ስታዲየም ሲጀመር የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጅራ፣ የስራ አስፈፃሚ አባል እና የከፍተኛ ሊግ ውድድር ሰብሳቢ አቶ ሙራድ ጨዋታዎቹን በክብር እንግድነት ተገኝተው አስከፍተዋል። ቤንች ማጂ ቡናን ከጋሞ ጨንቻ ባገነኘው የመጀመርያ ጨዋታ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በሙከራዎች ብልጫ የወሰዱት ቤንች ማጂ ቡናዎች በ26ኛው ደቂቃ ዘላለም በየነ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ በተከላካዮች መሐል ሾልኮ በማለጥ የቡድኑን ቀዳሚ ጎል አስገኝቷል። ጋሞ ጨንጫዎች ብልጫ ቢወሰድባቸውም አልፎ አልፎ አደጋ ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ስኬታማ ባይሆኑም ቤንች ማጂ ቡናዎችን ማስጨነቅ ችለው ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ቤንች ማጂ ቡናዎች በርከት ያሉ ዕድሎችን በሀሰን ሁሴን እና ተቀይሮ በገባው እሱባለው ሙልጌታ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ውስጥ 89ኛው ደቂቃ ሀሰን ሁሴን ሁለተኛውን ጎል ሲያስገኝ በተጨማሪ 92ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ዳንኤል አገኘው አማካኝነት የማሰረጊያ ሦስተኛ ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን በቤንች ማጂ ቡና 3–0 አሸናፊነት አጠናቀዋል።

ሰሜን ሸዋ ደብረብርሀን ከ ቂርቆስ ክ/ከ – ምድብ \’ለ\’

\"\"

የፌዴሬሽኑ የውድድር ዳይሬክተር አቶ ከበደ ወርቁ ባስጀመሩት ጨዋታ እና በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው የእንጂባ ተጫዋች ተስፋፂሆን ፋንቱ የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኋላ ከተያዘለት ሀያ አምስቱን ያህል ደቂቃዎች ዘግይቶ ነበር የሰሜን ሸዋ ደብረብርሃን እና ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጨዋታ የጀመረው። ረጅሙን ደቂቃ በቁጥጥር ብልጫ በመውሰዱ ረገድ ቂርቆሶች ሻል ቢሉም ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተዋቀሩት ደብረብርሃኖች ባደረጉት ጥንቃቄ አዘል አጨዋወት በቀዳሚው አርባ አምስት 26ኛው ደቂቃ ላይ የተሻ ግዛው ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቅጣት ምት ቢያድግልኝ ኤልያስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አሳርፎ ደብረብርሃንን መሪ አድርጓል። ቂርቆሶች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላም ቢሆን በይበልጥ በአንድ ሁለት ቅብብል በተደጋጋሚ የደብረብርሃንን ተከላካይ ሰብሮ ለመግባት ጫናን ሲያሳድሩ ቢታይም የሚያገኟቸውን ዕድሎች የግቡ ብረት እና ግብ ጠባቂው ደረጀ ዓለሙ ተጋግዘው ከጎልነት አትርፈዋቸዋል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ቂርቆሶች ተጨማሪ የተጫዋቾች ቅያሪን አድርገው በአማካዩ ጅብሪል ናስር እየተመሩ ልዩነት ለመፍጠር በእጅጉ ተግተዋል። 79ኛው ደቂቃ ላይ ቢያድግልኝ ኤልያስ በሳጥን ውስጥ ጅብሪል ናስር ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት የአቡበከር ናስር ታላቅ ወንድም ጅብሪል በራሱ ላይ የተሰራውን ጥፋት መትቶ ደረጀ ዓለሙ መልሶበታል። ከግቧ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ሽግግር ጨዋታው ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ኤልያስ ማሞ በጥሩ ዕይታ የሰጠውን ወንድወሰን ሽፈራው ግብ አድርጓት ጨዋታ በ2-0 የደብረብርሃን አሸናፊነት ተገባዷል።

የካ ክ/ከ ከ ስልጤ ወራቤ – ምድብ \’ሐ\’

በባቱ ከተማ የሚካሄደው የምድብ \’ሐ\’ የሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ አቶ ቃበቶ አማኖ የወጣቶች እና ስፖርት ኃላፊ ፣ አቶ አብዱላማን አደም የከንቲባ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ፣ አቶ ደረጄ ተረቦ የየካ ክ/ከተማ ወጣቶች እና ፅህፈት ቤት ኃላፊ እና አቶ በቀለ አበራ የውድድሩ እና የሥነ-ስርዓት ኮሚቴ በተገኙበት ተጀምሯል።

የዕለቱ ቀዳሚ የነበረው የየካ እና ስልጤ ወራቤ ከተማ የመጀመሪያው አጋማሽ እንደተጀመረ ባሉበት ደቂቃዎች የስልጤ ወራቤ የበላይነት የታየበት እና የጨዋታው ብቸኛ ግብም በ2ኛ ደቂቃ የተቆጠረበት ነበር። ማቲያስ ኤልያስ በፈጣን እንቅስቃሴ የተገኘው አጋጣሚ ወደ ግብነት በመለወጥ ስልጤ ወራቤን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ በብስራት በቀለ የሚመራው የየካ የፊት መስመር የስልጤ ወራቤ የተከላካይ ክፍልን በተደጋጋሚ ሲረብሽ ተስተውሏል። በስልጤ ወራቤ በኩል የተከላካይ ክፍሉ እና የመሀል ክፍሉ ጠንካራ ጥምረት በመጀመሪያ አጋማሽ ተስተውሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ የየካ የበላይነት የታየበት ሲሆን በአንፃሩ ስልጤዎች አፈግፍገው ለመጫወት ተገደዋል። በአጋማሹም ስልጤ ወራቤዎች የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃ ግብ ለማስቆጠረ የሞከሩ ቢሆንም ምንም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በስልጤ ወራቤ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የ05:00 ጨዋታዎች

አዲስ ከተማ ክ/ከ ከ ሰንዳፋ በኬ – ምድብ \’ሀ\’

በምድብ \’ሀ\’ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የነበረው አዲስ ከተማ ክ/ከ ከሰንዳፋ በኬን መካከል ተከሂዷል። በእንቅስቃሴ ደረጃ የተሻለ ሆነው የታዩት አዲስ ከተማዎች ብልጫ በወሰዱባቸው አጋጣሚዎች ወደ ጎልነት መቀየር የሚያስችሉ ጥቃቶችን አለመሰንዘራቸው ዋጋ ሲያስከፍላቸው አስተውለናል። በአንፃሩ በጥንቃቄ እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ የቆዩት ሰንዳፋ በኬዎች የመጀመርያም የመጨረሻም ጎላቸውን 39ኛው ደቂቃ ላይ አንበላቸው ፍቃዱ ባርባ በጥሩ ሁኔታ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን
አጥቂው መሳይ ሰለሞን በድንቅ አጨራረስ በግንባሩ ባስቆጠረው ጎል ጨዋታውን አሸንፈው ወጥተዋል።

ጉለሌ ክ/ከ ከ ሻሸመኔ ከተማ – ምድብ \’ለ\’

ቀደም ያለው ጨዋታ በጊዜ አለመጠናቀቁን ተከትሎ ዘግይቶ መጀመር የቻለው ይህ ጨዋታ በጉለሌዎች ፈጠን ያለ የሽግግር እንቅስቃሴ የጀመረ ነበር። በዚህም ሒደት አምበሉ ጁንዴክስ አወቀ 3ኛው ደቂቃ ላይ ግልፅ አጋጣሚን አግኝቶ ታምራት ዳኜ አድኖበታል። ቀስ በቀስ ጨዋታውን ወደ መስመር ባዘነበለ እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በተሻለ ይደርሱ የነበሩት ሻሸመኔዎች በአብዱልቃድር ነስሩ የርቀት ሙከራ እና በአብዱልከሪም ቃሲም የቅጣት ምት ኳሶች ሞክረው ግብ ጠባቂው ኩክ ኩዊዝ በድንቅ ብቃቱ ከመለሰባቸው በኋላ ባደረጉት ሌላ ሙከራ ግብ አግኝተዋል። 41ኛ ደቂቃ ላይ ከቀኝ የሜዳው ክፍል ሳምሶን ተሾመ ሲያሻማ ጌትነት ተስፋዬ በግንባር በማስቆጠር ሻሸመኔን መሪ አድርጓል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ጉለሌዎች የበላይነት በመልሶ ማጥቃት በተለይ በመስመር በኩል በመጫወት በጁንዴክስ አወቀ ፉአድ ሱልጣን አማካኝነት ወደ አቻነት ለመምጣት ሙከራዎችን አድርገው በሻሸመኔው ግብ ጠባቂ ታምራት ዳኜ መክነዋል። ሻሸመኔዎች ሮብሰን በዳኔን 85ኛው ደቂቃ ላይ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ካጡ በኋላ ጥቅጥቅ ባለ መከላከል ኳስን ሲያገኙ በፈጣን ሽግግር ለመጫወት ቢሞክሩም በጭማሪ 90+4 ላይ ዳዊት ሽፈራው ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጉለሌን አቻ በማድረግ ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሻሸመኔ ከተማ ደጋፊዎች በዕለቱ ዳኛ ላይ ተቃውሞን ሲያሰሙ የነበረበት መንገድ በቀጣይ ሊታረም የሚገባው ድርጊት መሆኑን በዚሁ ለመጠቆም እንወዳለን።

\"\"

የ08:00 ጨዋታዎች

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ

በምድብ \’ሀ\’ የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአቃቂ ቃሊቲ ጨዋታ በንግድ ባንክ የበላይነት ተጠናቋል። ከጨዋታው ጅማሬ አንስቶ አደጋ መፍጠር የጀመሩት ንግድ ባንኮች በአስረኛው ደቂቃ የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል። አጥቂው አቤል ማሙሽ ከመሐል ሜዳ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ግብጠባቂውን በማለፍ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል።

ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት እና ልምድ
ያለው ግብ ጠባቂው ቢንያም ኦሼ ባይኖር ኖሮ ተጨማሪ ጎሎችን ማስተናገድ ይገባቸው የነበሩት አቃቂ ቃሊቲዎች ይህ ነው የሚባል አደጋ መፍጠር የቻለ ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ተጨማሪ ጎሎችን በማስቆጠር ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያሰቡት አሰልጣኝ በፀሎት ልዑል ሰገድ ያደረጉት የተጫዋች ለውጥ ተሳክቶላቸው የወደፊት ተስፈኛው ወጣት መሆኑን ባስመለከተን በረከት ግዛቸው የግል ጥረት ታክሎበት በ79ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን ጎለ በማስቆጠር ጨዋታውን 2-0 አሸንፈው ወጥተዋል።

ጅንካ ከተማ ከ እንጅባራ ከተማ – ምድብ \’ለ\’

ከቀትር በኋላ የቀጠለው የምድቡ ጨዋታ ጂንካ ከተማን ከእንጂባራ ያገናኘ ነበር። በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው የእንጅባራው ተከላካይ ተስፋፂሆን ፋንቱ ክለቡ እና የክለቡ ተጫዋቾቹ በድምሩ 215 ሺህ ብር ካበረከቱ በኋላ ጨዋታው ጀምሯል። በእንቅስቃሴ ረገድ አጋማሹን እንጅባራዎች ተሽለው መታየት ቢችሉም 41ኛው ደቂቃ ላይ ኑራ ሀሰን ጂንካን መሪ አድርጓል።

ከዕረፍት ተመልሶ ጨዋታው አሁንም የእንጅባራ ከተማዎች የእንቅስቃሴም ሆነ የግብ ሙከራቸው አንፀባርቆ የተስተዋለበት ነበር። በምትኩ ማመጫ እና የሺዋስ በለው ሙከራ በኋላ 71ኛው ደቂቃ ላይ በአብርሃም ምህረት አስደናቂ አጨራረስ ግብ አግኝተው ወደ አቻነት ቢመጡም ይስተዋልባቸው የነበረውን የመከላከል ድክመት መቅረፍ አለመቻላቸው አለምሰገድ አድማሱ 88ኛው ደቂቃ ላይ ጂንካን አሸናፊ ያደረገች ሁለተኛ ጎልን ከመረብ አዋህዶ ጨዋታው 2ለ1 ተጠናቋል።

ዳሞት ከተማ ከ ሀምበርቾ ዱራሜ – ምድብ \’ሐ\’

በምድብ \’ሐ\’ ከምሳ በኋላ በተደረገው የዳሞት እና የመሪው ሀምበርቾ ዱራሜ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ ሀምበሪቾ ዱራሜ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። ሆኖም ግን ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አቅንተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን የዳሞት ከተማ ግብ ጠባቂ ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ኳሶችን ሲያድን ተስተውሏል። በአጠቃላይ በጨዋታው ምንም ግብ ሳይቆጠር ሁለቱ ቡድኖች አንድ አንድ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። በውጤቱም መሰረት የምድቡ መሪ የሆነው ሀምበርቾ ዱራሜ ከተከታዩ ገላን ከተማ ያለውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት የሙችልበትን ዕድል አምክኗል።

የ10:00 ጨዋታዎች

በምድብ \’ሀ\’ ሀላባ ከታማ እና ቡታጅራ ከተማ ያደርጉት የነበረው ጨዋታ ቡታጅራዎች ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።

ከፋ ቡና ከ አዲስ አበባ ከተማ – ምድብ \’ለ\’

የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ በዝናብ ታጅቦ 10 ሰዓት ሲል መሪው አዲስ አበባ ከተማን ከካፋ ቡና አገናኝቷል። ከመስመር መነሻቸውን በማድረግ የመዲናይቱ ተወካይ የማጥቂያ በሮችን ለመክፈት በኤርሚያስ ኃይሉ እና ሙሉቀን ታሪኩ አማካኝነት ዕድሎችን ፈጥረው ቢታይም ወደ ግብነት አልፈው ጎልን ለማግኘት ግን የካፋውን ግብ ጠባቂ ምንተስኖት አሰግድን ለመድፈር አልቻሉም። በእሸቱ መና የቅጣት ምት እና በመልሶ ማጥቃት በከድር ሲራጅ ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎችን ካፋዎችን አግኝተው የነበረ ቢሆንም ከጨዋታው ደብዛዛነት አንፃር ኳስ እና መረብ ተገናኝተው ሳንመለከት ያለ ግብ ተቋጭቷል።

ሮቤ ከተማ ከ ገላን ከተማ – ምድብ \’ሐ\’

በምድብ \’ሐ\’ የዕለቱ የመጨረሻ በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ገላን ከተማዎች ሙሉ በሙሉ ጨዋታውን በመብለጥ ጫና ያሳደሩ ሲሆን ሮቤ ከተማዎች ወደ ኋላ በማፈግፈግ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። በ30ኛው ደቂቃ ገላኖች ያገኙትን የግብ ዕድል በሱፍቃድ ነጋሽ ድንቅ በሆነ ሁኔታ በመጨረስ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና ፈጣን እንቅስቃሴ የተመለከትን ነበር። ሮቤ ከተማዎች የተወሰደባቸውን የግብ ብልጫ ለማስተካከል የጣሩ ቢሆንም ነገር ግን ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በአንፃሩ ገላን ከተማዎች በ82ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን የግብ ዕድል በኢብራሂም ባዱ አማካኝነት ወደ ግብ በመቀየር አሸናፊነታቸውን ማረጋገጥ ያስቻለ ግብ አስቆጥረዋል። ጨዋታው በገላን ከተማ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከመሪው ሀምበርቾ ዱራሜ ጋር ያለውን ርቀት ወደ ሁለት ነጥብ ዝቅ ማድረግ ችሏል።