የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ሞሮኮ ላይ ዛሬ ዝግጅቷን ትጀምራለች

መጋቢት 15 እና 18 ከኢትዮጵያ ጋር የምትጫወተው ጊኒ ከትናንት ጀምሮ ተጫዋቾቿ እየተሰባሰቡ ይገኛሉ።

ባለንበት የ2023 ዓመት የሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ የአህጉራችን ብሔራዊ ቡድኖች በምድብ ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን እያደረጉ እንደሚገኝ ይታወቃል።

\"\"

በምድብ አራት ከሀገራችን ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ማላዊ ጋር የተደለደለችው የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጊኒ የፊታችን ዓርብ እና የዛሬ ሳምንት ከኢትዮጵያ ጋር ወሳኝ የምድብ 3ኛ እና 4ኛ ጨዋታዎች ያሉባት ሲሆን ለእነዚህ ፍልሚያም የቡድኑ አሠልጣኝ ካባ ዲያዋራ ከቀናት በፊት ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ አስተላልፈዋል።

ከግብ ዘቡ ካማራ ሙሳ ውጪ በስብስቡ ሁሉም ተጫዋቾች ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ሲሆን በትናትናው ዕለትም ጨዋታዎቹ የሚደረጉበት ሞሮኮ መሰባሰብ ጀምረዋል። ከተጫዋቾቹ ቀድመው ዋና አሠልጣኙ ዲያዋራን ጨምሮ አጠቃላይ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት ቅዳሜ ከተሰባሰቡ በኋላ ነው በማግስቱ ተጫዋቾች በሞሀሚዲያ እየገቡ የሚገኘው። ትናንት ስብስቡን ያልተቀላቀሉ ተጫዋቾች ዛሬ ወደ ሞሮኮ እንደሚገቡ ሲጠቆም ቡድኑም ረፋድ ላይ ለኢትዮጵያ ጨዋታ ልምምዱን እንደሚጀምር ተመላክቷል።

\"\"