የከፍተኛ ሊግ ሦስተኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

ሦስተኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ሰባት ጨዋታዎች ተደርገዋል። ሶከር ኢትዮጵያም በስፍራው የተገኘችበት ምድብ ለ ላይ አተኩራ የዛሬን ውሎ እንዲህ ተመልክታለች። 

አስቀድሞ በሦስት ሰዓት በጀመረው የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ በወጣት ተጫዋቾች የተገነባው ኮልፌ ቀራንዩ ክፍለ ከተማ በጠባብ ውጤት ለገጣፎን ማሸነፍ ችሏል። ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እምብዛም የጎል ሙከራ ሳያስመለክተን ተከናውኗል። ኳሱን በመቆጣጠር እረገድ የተሻሉ የነበሩት ኮልፌዎች አልፎ አልፎ ወደ ፊት ቢሄዱም በቡድኑ ውስጥ ጨራሽ አጥቂ ባለመኖሩ በቀላሉ ኳሶች ይባክኑባቸው ነበር። በአንፃሩ ጣፎዎች በረጃጅም ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ቢሞክሩም ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጎል ዕድል መፍጠር ሲሳናቸው ተመልክተናል።

ከእረፍት መልስ በተመሳሳይ የጎል ዕድሎችን አንመልከት እንጂ ኮልፌዎች በተሻለ መንቀሳቀስ በቻሉበት አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት የተገኘውን ኳስ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ በኃላም በሲዳማ ቡና የተጫወተው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ እሱባለው ሙሉጌታ ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ግሩም ጎል ቺፕ በማድረግ ለኮልፌ ብቸኛውን ጎል ማስቆጠር ችሏል። ጣፎዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኃላ የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ቢያደርጉም ጠንክረው ሲከላከሉ የነበሩት የኮልፌዎችን ሰብረው ማለፍ አቅቷቸው ለመሸነፍ ተገደዋል። ውጤቱን ተከትሎም ኮልፌዎች የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

በመቀጠል ረፋድ ላይ የተካሄደው የቡራዩ ከተማ እና የቂርቆስ ጨዋታ በቡራዮ አሸናፊነት ተጠናቋል። ከዚህ ቀደም በተለያዩ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ሲጫወቱ የምናቃቸው ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች የተሰባሰቡበት ቂርቆሶች በመጀመርያው አጋማሽ የጎል እድል መፍጠር የቻሉት አንድ ግዜ ብቻ ነው። በቂርቆስ በኩል በግሉ ጎል ለማስቆጠር ይጥር የነበረው ሙከረም አለቱ ከመስመር የተሻገረለት ኳስ በቀጥታ ወደ ጎል መቶ የግቡ አግዳሚ የተመለሰበት አጋጣሚ ተጠቃች ነው። ቡራዩ ከተማ ባሳለፍነው ዓመት በአንደኛ ሊግ ውድድር ቆይታቸው ጥሩ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው አጥቂው ጫላ በንቲ ላይ ትኩረት ያደረገው አጨዋወታቸው ውጤታማ ነበር። ይህም ወደ ውጤት ተቀይሮ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የሚገኘወረ ጫላ ወደ ጎልነት ቀይሮ ቡራዩ ቀዳሚ አድርጓል። ከጎሉ መቆጠር በኃላ ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል ካሚል አህመድ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ግብጠባቂው አድኖበታል።

ከእረፍት መልስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው ቢጫወቱም ጅላሎ ሻፊ እና አስራት ሸገሬ በተገቢው መንገድ ያልተጠቀሙባቸው ኳሶች መባከናቸው ቂርቆሶችን ዋጋ አሰክሏቸዋል። በዚህም ምክንያት የቡራዮን ተከላካዮች ከማስጨነቅ ውጭ ብዙም አደጋ ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።

ሙሉ ለሙሉ ውጤቱን ለማስጠበቅ አፈግፍገው ሲጫወቱ የቆዮት ቡራዮዎች በመልሶ ማጥቃት የሚደርጉት ጫና ጎል አያስቆጥሩ እንጂ ስኬታማ ነበሩ። በአንድ አጋጣሚ በፍጥነት ወደ ፊት በመሄድ ከመስመር የተሻገረውን በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ ከሳጥን ውጭ ቆሞ የነበረው ቶሎማ ንጉሴ ወደ ጎል ቢመታውም አግዳሚው የመለሰው የሚያስቆጭ ነው። በቡራዩ በኩል ተቀይሮ በመግባት በእንቅስቃሴው ልዮነት የፈጠረው ጴጥሮስ ፀጋዬ ከአንድ ተጫዋች ጋር በመጋጨቱ አፍንጫው በመድማቱ መለያ ልብሱ በደም ይበከላል፤ በዚህ የተነሳ ሌላ ቀይሮ የሚለብሰው መለያ በማጣቱ ምክንያት ተመሳሳይ ቁጠር ለመፈለግ አንዴ በብዕር እዴ በፕላስተር ለጥፎ ለመግባት የሚደረገው ሩጫ ከህግ አንፃር ተቀባይነት አለማግኘቱ እና በዚህ ምክንያት የፈጀው ከአምስት ደቂቃ በላይ ጊዜ የጨዋታው አስገራሚ ክስተት ሆኖ አልፏል። በመጨረሻው ጨዋታው የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በቡራዩ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው ቡታጅራ ከተማን ከስልጤ ወራቤ ያገናኘው ጨዋታ ደመቅ ባለ የደጋፊ ድባብ ታግዞ በቡታጅራ አሸነፊነት ተጠናቋል።

ጥሩ ፉክክር ማሳየት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና ከጅምሩ ቀልብን የገዛ ነበር። የመስመር ተከላካዩ በጋሻው ክንዴ በጥሩ ሁኔታ የመታውን እና ግብጠባቂ ያወጣበት ቡታጅራ በኩል የጨዋታው የመጀመርያው የጎል ሙከራ ነበር። ጨዋታው የደርቢነት ስሜት ያለው በመሆኑ በሁለቱም በኩል ጉሽሚያ የበዛበት መሆኑ የዕለቱን ዳኛ ስራ ያበዛባቸው ሲሆን የጨዋታውንም መልክ በተደጋጋሚ ይቀይረው ነበር። ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የተቸገሩት ወራቤዎች ግልፅ በሆነ መንገድ ወደ ጎል ለመድረስ ሲቸገሩ እንዲሁም ተሻጋሪ የሆኑ ኳሶች ሲባክኑ አይተናል።

የመጫወት ፍላጎታቸው ከፍተኛ የሆኑት እና በመስመር አጨዋወታቸው ውጤታማ የነበሩት ቡታጀረራዎች የመጀመርያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ እንዳለማው ታደሰ ጎል አስቆጥሮ መምራት ችለዋል። ከእረፍት መልስ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ፍለጋ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ወራቤዎች በተለይ በኃይሉ ወገኔ አማካኝነት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ፈጥረው ግብጠባቂው አድኖባቸዋል።

በጥንቃቄ መከላከል ውስጥ ጥቃት የሚሰነዝሩት ቡታጅራዎች የቀድሞ የባህር ዳር ከተማው የመስመር አጥቂ ወሰኑ አሊ ከምናቀው የተለምዶ ቦታው በተለየ መንገድ አማካይ በመሆን የጨዋታውን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር እና ተገቢ የሆኑ ኳሶችን ለቡድን አጋሮቹ በማቀበል የነበረው ሚና የጎላ ነበር። የዕለቱ ዋና ዳኛ እና በተለይ በኩቡር ትሪቩን የነበሩት ረዳት ዳኛ መካከል በነበረው አለመናበብ የሁለቱንም ቡድኖች ያላስደሰተ ሆኖ የቀጠለው ጨዋታ በመጨረሻም በቡታጅራ አንድ ለምንም አሸነፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ቡታጅራ ከተማ ለጊዜውም ቢሆን የምድቡ መሪ መሆን ችሏል።

የዚህ ምድብ ጨዋታዎቹ ነገ ሲቀጥሉ 5:00 ከፋ ቡና ከ ከምባታ ሺንሺቾ፤ 9:00 ቤንች ማጂ ቡና ከ ሰንዳፋ በኬ የሚጫወቱ ይሆናል።

ሆሳዕና እየተደረገ በሚገኘው ምድብ ሀ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን ነጌሌ አርሲ አቤል ማሙሽ እና ምትኩ ጌታቸው ባስቆጠራቸው ጎሎች ሻሸመኔን 2-0 ሲያሸንፍ 10፡00 ላይ ሀላባ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል።

ጅማ ላይ እየተከናወነ በሚገኘው በምድብ ሐ በተመሳሳይ ሁለት ጨዋታ ተካሂደው ነቀምቴ ከተማ በሜዳው ጨዋታ እያደረገ የሚገኘው ጅማ አባ ቡናን 2-1 በመርታት በድንቅ አጀማመሩ ቀጥሏል። ኢብሳ በፍቃዱ እና ጌታሁን ባፋ ለነቀምቴ ሲያስቆጥሩ ማታይ ሉል የጅማን ጎል አስቆጥራል። ድሉን ተከትሎ ነቀምቴ በሙሉ 9 ነጥቦች ሊጉን እየመራ ይገኛል።

ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከ ወላይታ ሶዶ ከተማ ያደረጉት ሌላው የምድቡ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።