ጅማ አባ ጅፋር ምክትል አሠልጣኙ ላይ ውሳኔ አስተላልፏል

ከአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር በመሆን ጅማ አባ ጅፋርን ከወራት በፊት የተቀላቀሉት ምክትል አሠልጣኝ በክለቡ ቦርድ አዲስ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባለ ድል ጅማ የሀገሪቱን ከፍተኛ የሊግ ዕርከን ዋንጫ ካዝናው ውስጥ ካደረገ በኋላ በወጥነት የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ መዝለቅ አቅቶት ከዓመት ዓመት በወራጅ ቀጠናው እየዳከረ ይገኛል። በዘንድሮ የውድድር ዓመትም ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ የተለያዩ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቢቀላቅልም (አሠልጣኙ የምፈልፋቸውን ተጫዋቾች አላገኘሁም ቢሉም) አንድም ጨዋታ ሳያሸንፍ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።

ድረ-ገፃችን ከዚህ በፊት በዘገበችው መሠረትም ዋና አሠልጣኙ አሸናፊ በቀለን ጨምሮ የቡድኑ የአሠልጣኝ አባላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ እና ክለቡን ካለበት ደረጃ እንዲያሻሽሉ ኅዳር 28 በተፃፈ ደብዳቤ ቦርዱ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ባገኘነው መረጃ ደግሞ ምክትል አሠልጣኙ ኢያሱ መርሀጽድቅ (ዶ/ር) ከዋና ቡድን ኃላፊነታቸው እንዲነሱ ወስኗል።

በትናንትናው ዕለት አሠልጣኙ በእጃቸው የደረሳቸው ደብዳቤ “ክለቡ በዘንድሮ የውድድር ዓመት በማስመዝገብ ላይ ያለው ውጤት ምንም የመሻሻል እና የነጥብ ለውጥ ለማምጣት አዳጋች እየሆነበት በመሆኑ ምክንያት በሙሉ ትኩረት በተስፋ ቡድኑ ላይ መስራት እንዳለብን የክለቡ ቦርድ ስላመነ ይህንን የተስፋ ቡድን ባሉት የአሠልጣኝነት ሙያ እንዲያገለግሉ ተወስኗል።” ይላል።

ይህንን ተከትሎ አሠልጣኝ ኢያሱ ሀዋሳ የሚገኘውን ዋናውን ቡድን ለቀው በክለቡ የመቀመጫ ከተማ (ጅማ) የሚገኘውን የተስፋ ቡድን ተቀላቅለው በአምስተ ቀናት ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርጉ እና ስራቸውን እንዲጀምሩ ተመላክቷል።