የአራቱ ተጫዋቾች እና ሀድያ ሆሳዕና የክስ ሂደት ወደ ሌላ ምዕራፍ ተሻግሯል

በአራቱ ተጫዋቾች እና በሀድያ ሆሳዕና የክስ ጉዳይ ዙሪያ አዲስ ነገር ተሰምቷል።

ያሳለፍነው ዓመት በቅድመ ስምምነታችን መሠረት ሊከፈለን የሚገባ ከሁለት ሚልየን ብር በላይ አልተሰጠንም በማለት ሱሌይማን ሀሚድ ፣ አክሊሉ አያናው ፣ አማኑኤል ጎበና እና ብሩክ ቀልቦሬ አቶ ብርሐኑ በጋሻው የሕግ አማካሪ ጠበቃ እና የአግር ኳስ ስፖርትኞች ሕጋዊ ወኪል ጠበቃ አድርገው በመቅጠር ልደታ 5ኛ ፍ/ብሔር ችሎት ጉዳያቸው እየታየ ቆይቷል።

ጉዳዩን እየተመለከተው የሚገኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት በገላጋይ ኮሚቴ በሽምግልና እንዲታይ ቀጠሮ እየተጠበቀ ባለበት ወቅት ሀድያ ሆሳዕና 60% በሁለት ወር ውስጥ ከፍለን የቀረውን በሌላ ጊዜ እንክፈል በማለት ለፍርድ ቤቱ ሀሳብ ያቀረበ ቢሆንም የተጫዋቾቹ ጠበቃ አቶ ብርሀኑ በጋሻው ክለቡ ያቀረበውን ሀሳብ አንቀበልም በማለታቸው ዛሬ ፍርድ ቤቱ ክስ ለመስማት ሁሉቱንም ወገኖች ጠርቶ ነበር።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሀድያ ሆሳዕና ሥራ አስኪያጅ ለፍርድ ቤቱ ክስ ከመስማቱ ይልቅ ለሽምግልናው አንድ ዕድል እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሠረት ተከታዩን ሀሳብ አቅርበዋል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉትቦለርስ አሶሴሽን ፕሬዝደንት አሰልጣኝ ዮሐንስ ሰህሌ ለመጨረሻ ጊዜ በሽምግልና እንዲያደራድሩን እንጠይቃለን በማለት መፍትሄ አቅርበዋል። ይህንንም ሀሳብ የተጫዋቾቹ ጠበቃ ተስማምተው የተቀበሉት በመሆኑ ፍርድ ቤቱም ከቀጠሮ በፊት እስከ ታህሳስ 20 ድረስ ተስማምተው እንዲቀርቡ ወስኖ ያልተስማሙ ከሆነ ግን ክስ ለመስማት ለታህሳስ 25 ቀጠሮ ሰጥቶ ተለያይተዋል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በአሸማጋይነት የገቡበት ይህ ጉዳይ መጨረሻው ምን እንደሚሆን ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።