ሪፖርት | ዐፄዎቹ በሰንጠረዡ አናት ሆነው ወደ ዕረፍት አምርተዋል

በዘጠነኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ መከላከያን 1-0 ማሸነፍ የቻለው ፋሲል ከነማ አንደኝነቱን ማስጠበቅ ችሏል።

መከላከያ ከሲዳማው ጨዋታ ደሳለኝ ደባሽ እና ብሩክ ሰሙን በዳዊት ወርቁ እና ልደቱ ጌታቸው በመተካት ጨዋታውን ሲጀምር ፋሲል ከነማ ከባህር ዳር ጋር የተጠቀመውን አሰላለፍ ሳይለውጥ ወደ ሜዳ ገብቷል።

ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ሚኬል ሳማኬ ኳስ ለመወርወር ሲሞክር በሰራው ስህተት አቤል ነጋሽ ያገኘውን ግልፅ ዕድል ያልተጠቀመበትን አጋጣሚ ተመልክተናል። ከዚህ በኋላ በአመዛኙ በሜዳቸው ያሳለፉት መከላከያዎች በቀጥታ ወደ ፊት ከሚልኳቸው ኳሶች ሌላ ሙከራ ማድረግ ከብዷቸው ታይቷል። የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን የወሰዱት ፋሲሎችም በሜዳው ስፋት በርከት ብሎ የሚከላከለው ተጋጣሚያቸውን በቅብብሎች ማለፍ ቀላል አልሆነላቸውም። ይልቁኑም ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ሳጥን መጣልን ሌላኛው አማራጭ አድርገው ወስደውታል። 6ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ አምሳሉ ጥላሀን የተሻማውን ኳስ በግንባሩ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራ በአጋማሹ ውስጥ ያሳዩት የተሻለው የግብ አጋጣሚ ነበር።

ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ ፋሲሎች ተደጋጋሚ የቆመ ኳስ ዕድሎችን በጦሩ ሳጥን ዙሪያ ቢያገኙም ሊጠቀሙበት አልቻሉ። ይልቁኑም ወደ አጋማሹ ማብቂያ ላይ በንፅፅር በፋሲል ሜዳ ላይ መታየት የቻሉት መከላከያዎች ከሌላ የፋሲል ስህተት ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። 39ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ባየህ እንቅስቃሴ ለማስጀመር ሲሞክር በተደረበ ኳስ አቤል ነጋሽ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ጠንካራ ሙከራ በሳማኬ ተይዞበታል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ኢብራሂም ሁሴን በሳጥኑ መግቢያ ላይ ኳስ በእጁ ሲነካ ‘ከውስጥ ወይስ ከውጪ ?’ የሚል ውዝግብ ተነስቶ በመጨረሻም ጨዋታው በፋሲል ከነማ ቅጣት ምት ቀጥሏል።

ከዕረፍት መልስ መከላከያዎች በተሻለ ድፍረት ለፋሲል ሳጥን ቀርበው መታየት ቢጀምሩም ዓለምብርሀን ይግዛው ከቀኝ ወደ ውስጥ ለማድረስ የሞከረውን ኳስ ቢኒያም ላንቃሞ በእጅ በመንካቱ ፋሲሎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። አጋጣሚውን ያሬዳ ባየህ 49ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አድርጎት አፄዎቹ መምራት ጀምረዋል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጨዋታው የተሻለ ክፍት ሆኖ ሁለቱም በቁጥር ብልጫ የማጥቃት ወረዳ ላይ የተገኙባቸውን አጋጣሚዎች ብናይም ወደ አደገኛ ሙከራነት ግን አልተቀየሩም። በሂደት የቀደመ ጫናቸውን ወደማግኘት የተቃረቡት ፋሲሎችም መካከለኛ ርቀት ያላቸውን ኳሶች ወደ ሳጥን ማድረስ ሲቀጥሉ ከኦኪኪ ክሌመንት ቦዬን የሚፈትን ሙከራ ሳያገኙ ቀርተዋል።

በጥሩ ፉክክር በቀጠለው ጨዋታ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ወደ 4-4-2 የመጡት መከላከያዎች ወደ ፊት በሚልኳቸውን ኳሶች ከቀደመው የተሻለ አደጋ የመፍጠር ምልክት ታይቶባቸዋል። ወደ ቀኝ ያደላው የፋሲሎች ጥቃት ግን ይበልጥ ለሙከራዎች የቀረበ ነበር። በጭማሪ ደቂቃዎች ጦሩ ከቆሙ ኳሶች ጫና ለመፍጠር ያደረገው ጥረት እና የፋሲሎች የመስመር ጥቃት የፍፃሜውን ግለት ቢጨምርለትም ሁለቱ ግብ ጠባቂዎችን የሚያስጨንቁ ሙከራዎች ሳንመለከት ጨዋታው ተቋጭቷል።

በውጤቱ ፋሲል ከነማ ነጥቡን 18 በማድረስ ለአፍሪካ ዋንጫ የሚቋረጠውን ሊግ ከላይ ሆኖ መምራቱን አረጋግጧል።