ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና የኢትዮጵያ ቡናን ተከታታይ የማሸነፍ ጉዞ ገቷል

በምሽቱ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና የኢትዮጵያ ቡናን ለአራት ጨዋታዎች የዘለቀውን የማሸነፍ ጉዞን በፍሬዘር ካሳ ብቸኛ የግንባር ኳስ ግብ በማሸነፍ መግታት ሲችሉ በሦስተኛ ተከታታይ ድላቸው ደረጃቸውንም አሻሽለዋል።

ሁለቱም ቡድኖች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ድል ካደረጉት ቡድኖቻቸው ላይ አንድ አንድ ለውጥ ያደረጉ በኢትዮጵያ ቡና በኩል ያብቃል ፈረጃ ወጥቶ በምትኩ አቤል እንዳለ የገባ ሲሆን የሀዲያ ሆሳዕና ለውጥ ፊት መስመር ላይ ባዬ ገዛኸኝን አስወጥተው በኡመድ ኡኩሪ ተክተው ወደ ጨዋታው ገብተዋል።

ለቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች በነበረው እና በአሁኑ ወቅት በሀዲያ ሆሳዕና ለሚገኘው እያሱ ታምሩ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ባበረከቱት የማስታወሻ ስጦታ የጀመረው ጨዋታ የተነቃቃ የሜዳ ላይ ፉክክርን ተመልክተናል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከፍ ብለው ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ እንዳይመስርቱ ጫና በማሳደር ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ቡናዎች በረጃጅም ኳሶች እና በፈጣን ሽግግሮች ወደ ሆሳዕና የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶች ሲደረጉ በስፋት አስተውለናል።

በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የተጠጉባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም በአጋማሹ ምንም አይነት ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራን ያልተመለከተንበት አጋማሽ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዲያ ሆሳዕናዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ላይ ከፍ ብለው ኳሶችን ጫና ፈጥሮ ለመንጠቅ ከመሞከር ይልቅ መሀል ሜዳ በቁጥር በርከት ብለው ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ በነፃነት ተቀባብለው እንዳይወጡ ለማድረግ ጥረት ያደረጉ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናዎች ይህን በቁጥር የበዛውን የሀዲያን የመሀል መስመር ለማለፍ በጣም ተቸግሮ አምሽቷል።

በ62ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው የመጀመሪያ በነበረው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ፍሬዘን ካሳ ሳምሶን ጥላሁን ወደ ግራ ካደላ አቋቋም የተሻማለትን የቆመ ኳስ በግንባር በመግጨት ሆሳዕናን ቀዳሚ ያደረገችን ግብ አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ ኢትዮጵያ ቡናዎች የመሀል ሜዳ ላይ የነበረባቸውን ኳስ የማሳደግ ችግር ለመቅረፍ በጫና ውስጥ ኳሶችን በመቀበል እና በማቀበል የተሻለ የሆነውን ታፈሰ ሰለሞን በማስገባት ሙከራ ቢያደርጉም ጥረታቸው ብዙም ፍሬያማ አልነበረም።

በሂደት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ይበልጥ ወደ ግባቸው ቀርበው መከላከል መጀመራቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ቀኝ መስመር ወጥቶ ለመጫወት በተገደደው ዊልያም ሰለሞን የግል ክህሎትን መሰረት ባደረጉ እንቅስቃሴዎች እድሎችን ለመፍጠር ቢታትሩም ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጨዋታው በሆሳዕናዎች አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ በ12 ነጥብ ወደ ሰባተኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችሉ ኢትዮጵያ ቡናዎች በ14 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።