የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጊኒ ተሸንፏል

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሦስተኛ የምድብ ጨዋታቸውን ከጊኒ ጋር ያደረጉት ዋልያዎቹ 2-0 ተረተዋል።

\"\"

በፈጣን እንቅስቃሴ የጀመረው የመጀመርያው አጋማሽ የጊኒ ብሄራዊ ቡድን ሙሉ ብልጫ የታየበት ነበር። ፍራንሲስ ካማኖ ከሳጥን ጠርዝ መትቶ በወጣበት ኳስ ጥቃታቸው የጀመሩት ጊኒዎች በፍራንኮይስ ካማኖ ፣ መሐመድ ባዮ እና ኬታ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገዋል። በተለይም ካማኖ መቷት አግዳሚው የመለሳት ለግብ የቀረበች ነበረች።

39ኛው ደቂቃ ላይም በግሉ በርካታ ሙከራዎች ያደረገው ፍራንኮይስ ካማኖ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ጊኒዎች ከግቧ በኋላም የሰይድ ሀብታሙ ምርጥ ብቃት ባይታከልበት በኬታ አማካኝነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በዋልያዎቹ በኩልም አቤል ያለው ያደረጋት ብቸኛ ለግብ የቀረበች ሙከራ ትጠቀሳለች።

በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ቅያሬ ያደረጉት ዋልያዎቹ እንደ መጀመርያው አጋማሽ የተጋጣሚ ጫና ተቋቁመው ለመጫወት ሲከብዳቸው ተስተውሏል።
የአጨራረስ ድክመት የነበራቸው ጊኒዎችም በርካታ ዕድሎች አምክነዋል። ሆኖም 72ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ ባዬ በመልሶ ማጥቃት ሄዶ ግሩም ግብ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱ ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።

ከግቡ በኋላም መነቃቃት ያልቻሉት ዋልያዎቹ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩ ነበር ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ የቻሉት። ሙከራውም በአቤል ያለው አማካኝነት የተደረገ ነበር።

ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁ ተከትሎ በምድቡ ጊኒ እና ግብፅ ነጥባቸው ወደ ስድስት ከፍ ስያደርጉ ኢትዮጵያ እና ማላዊ በነበሩበት ረግተዋል።

\"\"