​ዋልያዎቹ ነገ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደርጋሉ

ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅቱን በካሜሩን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንደሚያደርግ ታውቋል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጥር 1-29 ድረስ በካሜሩን በሚከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ እንደሚሳተፍ ይታወቃል። ቡድኑም ለዚሁ አህጉራዊ ውድድር ያሳለፍነው እሁድ ወደ ስፍራው አምርቶ ዝግጅቱን እያከናወነ ሲሆን በነገው ዕለትም ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጋር የመጀመሪያ የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በውድድሩ ከሚሳተፉ 24 ቡድኖች አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው እሁድ እና ሰኞ ካሜሩን የደረሱት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ዛሬን ጨምሮ ያለፉትን ቀናት ልምምዳቸውን ሲሰሩ የነበረ ሲሆን በነገው ዕለትም የእርስ በእርስ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከነገው ጨዋታ በፊት የመጨረሻ ልምምዱን ቀትር ላይ ሲሰራ የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ረፋድ ላይ ቀለል ያለ ልምምድ አከናውኗል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታም ነገ 11:30 የሚደረግ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው ዕለት ከሱዳን ጋር የመጀመሪያ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ካከናወነ በኋላ ደግሞ ውድድሩ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከአንድ ወይም ሁለት ተጨማሪ ቡድኖች (ምናልባት ከምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች) ጋር ሌላ ጨዋታ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።