“በአፍሪካ ዋንጫው ሀገሬን ለማስጠራት በመመረጤ ደስ ብሎኛል” የካፍ ኤሊት ኢንስትራስተር አብርሃም መብራቱ

በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የካፍ የቴክኒክ ኮሚቴ አባል በመሆኑ ተመርጠው ወደ ስፍራው ከማምራታቸው በፊት የተሰማቸውን ስሜት ለሶከር ኢትዮጵያ አጋርተዋል።

33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር በካሜሩን አስተናጋጅነት ከጥር 1 ጀምሮ በሀያ አራት ብሔራዊ ቡድኖች መካከል ይደረጋል። ከስምንት ዓመታት በኋላ ሀገራችን ኢትዮጵያ ዳግም በዚህ ትልቅ መድረክ ላይ ተካፋይ የምትሆን ሲሆን ኢትዮጵያም ወደዚህ መድረክ እንድታልፍ የራሳቸውን ድርሻ ከተወጡ አሰልጣኞች መሀል ዋልያዎቹን ያሰለጠኑት የካፍ ኤሊት ኢንስራክተር አብርሃም መብራቱ ካፍ ካሏት 24 ኤሊት ኢንስራክተሮች መካከል አንዱ ናቸው። ከሰሞኑ ካፍ ለአፍሪካ ዋንጫ የቴክኒክ ዲፓርትመንት አዋቅሮ አስራ ሁለቱን ሲለይ ኢትዮጵያዊው ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ ሀገራችንን በመድረኩ በብቸኝነት ወክለው የፊታችን ሀሙስ ወደ ካሜሮን ያውንዴ ያመራሉ፡፡

የአፍሪካ ዋንጫው ከመጀመሩ ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ በሚሰጥ ስልጠና አሰልጣኙ የሚገመግሟቸውን ሀገራት የሚለዩ ሲሆን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት አሰልጣኙ ሀገራቸው ወክለው መጠራታቸው እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ፡፡

“በአፍሪካ ዋንጫው ሀገሬን ለማስጠራት በመመረጤ ደስ ብሎኛል። ይሄ ለእኔም ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በይበልጥ ደግሞ ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን በር የሚከፍትም ጭምር ነው፡፡ ሀላፊነቱ ቀላል አደለም። እጅግ ትልቅ ነው፡፡ ግብፅ ላይ የነበረኝን ጥሩ ስራ ካሜሩን ላይም ለመድገም ተዘጋጅቻለሁ” በማለት አጠር ያለ ሀሳባቸውን አጋርተውናል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ግብፅ ላይ በተደረገውም የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በተመሳሳይ ተግባር ተሳትፈው የነበሩት ኢንስትራክተሩ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና ከኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በአምላክ ተሰማ ቀጥሎ በካሜሩን ኢትዮጵያን ወክለው በመድረኩ የሚቀርቡም ይሆናል፡፡