​ፊፋ ግዙፉ የወልቂጤ የግብ ዘብ ላይ ውሳኔ አሳልፏል

የፊፋ ዲሲፕሊን ኮሚቴ አይቮሪኮስታዊውን ግብ ጠባቂ ሲልቫይን ግቦሆን በጊዜያዊነት እንዳገደ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በላከው መልዕክት አስታውቋል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሰራተኞቹን የተቀላቀለው ሲልቫይን ግቦሆ በዘንድሮ የቤንትኪንግ ፕሪምየር ሊግ 699 ደቂቃዎችን የተጫወተ ሲሆን በስምንተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ቡድኑ ወልቂጤ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቶ ነበር። ይህንን ተከትሎ ከሰበታ ከተማ ጋር የተደረገው የመጨረሻ ጨዋታም አምልጦት ነበር። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከፊፋ የዲሲፕሊን ኮሚቴ ደረሰኝ ብሎ አሁን ባወጣው መረጃ ደግሞ ተጫዋቹ በጊዜያዊነት ከውድድሮች መታገዱን ያመላክታል።

ፌዴሬሽኑ ያወጣው መረጃ የሚከተለው ነው :-

ለአይቮሪኮስት ብሔራዊ ቡድን እየተጫወተ የሚገኘው ሲልቫይን ግቦሆ በአሁኑ ወቅት በወልቂጤ ከተማ ተመዝግቦ እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን ኖቬምበር ላይ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ አይቮሪኮስት ከጋቦን ጋር ስትጫወት በእጣ የዶፒንግ ምርመራ እንዲሰራለት ወጥቶበት የሽንት ናሙና ሰጥቶ ነበር። በዚህ ናሙና ውስጥም ትራይሜታዚዲን የሚባል ከ2014 ጀምሮ አትሌቶች እንዳይጠቀሙት በዋዳ የታገደ ንጥረ ነገር ተገኝቷል።

ንጥረ-ነገሩ በደም ስር መጥበብ ምክንያት የሚመጣ የልብ በሽታዎችን ለማከም የሚጠቅሙ መድሃኒቶች ላይ የሚገኝ ሲሆን የልብ ጡንቻዎችን የግሉኮስ አጠቃቀም ያጎለብታል። በዚህ ምክንያትም በዓለም አቀፉ ፀረ-አበረታች መድሃኒት እና ቅመሞች ቁጥጥር ኤጀንሲ ጥቅም ላይ እንዳይውል ተከልክሏል። ለህክምናው ሌላ አማራጭ በማይኖርበት ጊዜ ይህንን በሐኪሞች በማረጋገጥ ‘ልዩ ለህክምና የመጠቀም ፈቃድ’ ወይም ‘Therapeutic Use Exemption’ (TUE) ከWADA በማግኘት መጠቀም የሚቻል ቢሆንም ሲልቫይን ግን ይህ ፈቃድ እንደሌለው ኤጀንሲው አስታውቋል። በህጉ መሰረትም ይህ ሲያጋጥም ወዲያው ጊዜያዊ ዕገዳ በተጫዋቹ ላይ ከተጣለ በኋላ በዲሲፕሊን ኮሚቴው የመጨረሻ ውሳኔ ከአጭር ጊዜ በኋላ የሚሰጥ ይሆናል።

በዚህም መሰረት የፊፋ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ተከታዩን ውሳኔ በተጫዋቹ ላይ አሳልፏል፦

1- ይህ ውሳኔ ከተገለጸበት ቀን ጀምሮ ሲልቫይን ግቦሆ በዓለም አቀፍ ደረጃ በጊዜያዊነት ይታገዳል

2- ይህ ጊዜያዊ እገዳ ሀገር አቀፍ ወይም ዓለም አቀፍ ውድድር ያካተተ ነው።

3- በፊፋ የፀረ-አበረታች መድሃኒት ህግ (2021 ed.) ውስጥ በተካተቱት ድንጋጌዎች መሰረት ቀደም ብሎ ካልተቋረጠ በስተቀር ጊዜያዊ እገዳው በፊፋ የዲሲፕሊን ኮሚሽን የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል።