​ዋልያዎቹ ሁለት ተጫዋቾቻቸውን እና አንድ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቸውን ከኮቪድ መልስ አግኝተዋል

ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ካሜሩን ሲያመራ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሁለት ተጫዋቾች ከቫይረሱ ማገገማቸው ሲታወቅ ለመጀመሪያ ጊዜም ዛሬ ልምምድ እንደሚሰሩ ታውቋል።

ጥር 1 ለሚጀምረው የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅቱን በካሜሩን ያውንዴ እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ስፍራው ሲያቀና ሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቹን እና አንድ የአሠልጣኝ ቡድን አባሉን በኮቪድ-19 ምክንያት አጥቶ ሲዘጋጅ እንደነበር ይታወቃል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ባሳለፍነው ሀሙስ ተጨማሪ አምስት ተጫዋቾች እና ሦስት የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱን በተመሳሳይ ምክንያት አጥቶ ነበር።

ሶከር ኢትዮጵያ ከስፍራው ባገኘችው መረጃ መሰረት ደግሞ ቡድኑ ስፍራው (ካሜሩን) ሲደርስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁለቱ ተጫዋቾች እና አንድ የአሠልጣኝ ቡድን አባላት በትናንትናው ዕለት ምርመራ ተደርጎላቸው ነፃ ሆነዋል። ይህንን ተከትሎም ከአንድ ሳምንት በኋላ ተጫዋቾቹ በዛሬው ዕለት ከአጋሮቻቸው ጋር የመጀመሪያ ልምምዳቸውን የሚሰሩ ይሆናል። ሀሙስ በቫይረሱ የተያዙት የቡድኑ አባላት ግን (አምስት ተጫዋቾች እና ሦስት የአሠልጣኝ ቡድን አባላት) በቀጣይ በሚኖር ምርመራ ነፃ መሆናቸው እንደሚለይ ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የስምንተኛ ቀን ልምምዱን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከ6 ሰዓት ጀምሮ የሚያከናውን ይሆናል።