​የዋልያዎቹን የምሽቱን ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ታውቀዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ያለውን ቆይታ የሚወስነውን የምሽቱን ተጠባቂ ጨዋታ የሚመሩ ዳኞች ይፋ ሆነዋል።

33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎችን ማድረግ በዛሬው ዕለት ይጀምራል። በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኬፕ ቨርድ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በሁለት የምድቡ ጨዋታዎች ሽንፈትን ቢያስተናግድም ወደ ጥሎ ማለፍ ለማለፍ ያለውን የመጨረሻ ዕድል በዛሬው ዕለት ይሞክራል። በዚህም ምሽት 1 ሰዓት ከቡርኪና ፋሶ ጋር ጨዋታውን የሚያከናውን ይሆናል።

ለዋልያው እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ይህንን ጨዋታም ሞሪሺየሳዊው ዳኛ አህመድ ኢምታዝ ሄራላል በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት ሞሮኮዋዊው አካርካድ ሞስጠፋ እና ናይጄሪያዊው ሳሙኤል ፕዋዱታካም በረዳትነት እንዲሁም ከሲሸልስ የመጡት በርናርድ ካሚሊ በአራተኛ ዳኝነት እንደሚመሩት ተረጋግጧል። ግብፃዊው መሐሙድ መሐመድ አሹር እና አልጄሪያዊው ላህሎ ቤንብራህማ በቪ ኤ አር ክፍል ውስጥ ሆነው ጨዋታውን እንደሚመሩ ተመላክቷል።

ዋልያው በመጀመሪያው የምድብ ጨዋታው ከኬፕ ቨርድ ጋር ተጫውቶ አንድ ለምንም በሆነ ጠባብ ውጤት ሲሸነፍ በ10ኛው ደቂቃ የቡድኑ ወሳኝ ተከላካይ ያሬድ ባየህ በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣቱ አይዘነጋም። በዕለቱ የመሐል ዳኛ የነበሩት አንጎላዊው ሄልደር ማርቲንስ ዲ ካርቫልሆ ያሬድ በሰራው ጥፋት ቀድመው ቢጫ ካርድ ቢሰጡትም የቪ ኤ አር ዋና አልቢትር የነበሩት ግብፃዊው መሐሙድ መሐመድ አሹር ዋና ዳኛው ጥፋቱን ደግመው ተመልክተው ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑት ምክረ ሀሳብ የሰጡት የቪ ኤ አር ዳኛው ዛሬም በቦታው ተሰይመዋል።