​አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል መግለጫ ሰጥተዋል

👉”እንደ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ምክትሎቼን በአግባቡ የመምረጥ ሀላፊነት አለብኝ”

👉”በልምምድ ወቅት ጉልበት የመጨረስ ነገር አይቻለው”

👉”ሀገሬን በጥሩ ነገር ማስጠራት እፈልጋለው”

ኮስታሪካ ለምታስተናግደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ብሔራዊ ቡድኖችን ለመለየት በየክፍለ አህጉሩ የማጣሪያ ጨዋታዎች እየተደረጉ እንደሆነ ይታወቃል። በአህጉራችን አፍሪካም ከቅድመ ማጣሪያ ጀምሮ ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን በውድድሩ የሚሳተፉ ሁለት ብሔራዊ ቡድኖችን ለመለየትም የአራተኛ እና የአምስተኛ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች ይቀራሉ። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድንም የሩዋንዳ እና የቦትስዋና አቻውን አሸንፎ ለአራተኛ ዙር ጨዋታ ከታንዛኒያ ጋር ተመድቧል። ለዚህ ወሳኝ ጨዋታ ከአስር ቀናት በፊት መዘጋጀት የጀመረው ቡድኑም እሁድ ላለበት የመጀመሪያ ጨዋታ በነገው ዕለት ወደ ስፍራው ያቀናል። ከጉዞው በፊት ደግሞ የቡድን ዋና አሠልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ስለ ዝግጅታቸው እና ስለጨዋታው በጣት የሚቆጠሩ የብዙሃን መገናኛ አባላት በተገኙበት ዛሬ ከሰዓት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

አሠልጣኙ “ማጣሪያውን ከጀመርን ቆይቷል። በመሐል የሴካፋም ውድድር ነበር። አሁን ላይ እንደ ሌላው ጊዜ ሰፊ የመዘጋጃ ጊዜ አላገኘንም። ተጫዋቾቹም ከውድድር ነው የመጡት። በልምምድ ወቅት ጉልበት የመጨረስ ነገር አይቻለው። ይህንን አይቼ ልምምዴን ቀነስ አድርጌ የሚያገግሙበትን መንገድ ለመፈለግ ጥሬያለው። ይሄ ቡድን በፊት የነበረው ቡድን ነው። እርግጥ አዳዲስ ተጫዋቾችም አሉ። ግን እንዳልኩት በአመዛኙ ከመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ጀምሮ ያሉ ተጫዋቾች ያሉበት ነው።” ካሉ በኋላ በዝግጅት ወቅት ተጫዋቾች ላይ ስለታየው ጉልበት የመጨረስ ጉዳይ ዘለግ ያለ ደቂቃ በመውሰድ ሀሳብ ሰጥተዋል።

“በፊት ካለው አንፃር አሁን ላይ አቅም የመጨረስ ነገር አይተናል። ይህንን ታሳቢ አድርገን ክፍል ውስጥም ሆነ በሜዳ ላይ የተሻለ ነገር ለመስራት ጥረናል። እንዳልኩት ግን አብዛኞቹ ተጫዋቾች ጉልበት ጨርሰው ነው የመጡት።” ሲሉ ይህንን ተከትሎ የተጫዋቾቹን ጉልበት ለማደስ ያደረጉትን ተግባር ተጠይቀው ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ሙያዊ እገዛ ያስፈልጋል። ብሔራዊ ቡድን እስከሆነ ድረስ ሙያዊ እገዛ ያስፈልጋል። ሀገሪቷን የሚደግፉ ሰዎች አሉ። ከእነርሱም ጋር ሀሳብ እንቀያየራለን። ከፌዴሬሽኑም ጋር መነጋገር የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እንዳልኩት የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቹ ከዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጀምሮ የተጫወቱ ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን በሊጉም ጨዋታዎችን አድርገዋል። ይህንን ተከትሎ ሪከቨር ለማድረግ ትንሽ ተቸግረናል። ግን የልምምድ መርሐ-ግብራችንን በማስተካከል የተባለውን ክፍተት ለመድፈን ጥረናል።”

በተከታይነት በዝግጅት ወቅት የልምምድ ሜዳዎችን ሲቀያይሩ የነበረበትን ምክንያት ተጠይቀው ማስረዳት የያዙት አሠልጣኙ “ያረፍንበት የካፍ የልህቀት ማዕከል የመጫወቻ ሜዳ ምቹ አይደለም። ተጫዋቾቹን ከመጠበቅ አንፃር ወደ 35 ሜዳ ሄደን ልምምድ አከናውነናል። ሰሞኑን ደግሞ በቦታው ሀይማኖታዊ በዓል ስለሚከበር እና ታንዛኒያ ላይ የምንጫወተው በአርቴፊሻል ሜዳ ስለሆነ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለመስራት ሞክረናል። ዛሬ ደግሞ በጊዮርጊስ ሜዳ ሰርተናል። ሜዳ ብቻ ሳይሆን የዐየር ሁኔታም እየታየ ልምምድ ይሰራል። ከዚህ ውጪ በስነ-ምግብ እና ስነ-ልቦና ረገድም ባለን አቅም ተጫዋቾቹን ለማብቃት ጥረናል።”

ለታንዛኒያው ጨዋታ ዝግጅት ሲያደርግ ምክትል አሠልጣኝ የለወጠው ቡድኑን በተመለከተም አሠልጣኝ ፍሬው “ከዚህ በፊት የግብ ጠባቂ አሠልጣኝ ሲለወጥ የጠየቀ የለም። አሁንም ተመልሶ የግብ ጠባቂው አሠልጣኝ ሲመጣ የጠየቀ የለም። ምክትል አሠልጣኟ ላይ ብቻ ትኩረት ተሰጥቷል። ይህ አግባብ አይደለም። ዋናው መታሰብ ያለበት ስለሀገር ነው። በተለይ ደግሞ ሴቶች በሙያው ልምድ እንዲያገኙ መደረግ አለበት ብዬ አምናለው። አሁን የመጣችው አሠልጣኝ በሙያው ልምድ ያላት እና እውቀቱ ያላት ነች። ስለዚህ መጥታ ልምድ እያገኘች ሀገሯን ብታገለግል ምንም ችግር የለውም። ወደፊትም ደግሞ እንደ እሷ አይነት ሰዎች እየመጡ ልምድ እንዲያገኙ የምናደርግበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል። ይህንን ስል ግን ሁሉንም እናዳርሳለን እያልኩኝ አደለም። እንደ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ደግሞ ምክትሎቼን በአግባቡ የመምረጥ ሀላፊነት አለብኝ።” ብለው ሀሳብ ሰጥተዋል።

በመጨረሻ ለዓለም ዋንጫው ለማለፍ ስላለቸው ቁርጠኝነት እና ስለታንዛኒያው ጨዋታ የተጠየቁት አሠልጣኙ  “ሀገሬን በጥሩ ነገር ማስጠራት እፈልጋለው። በሴካፋ የመጣውን ነገር ታውቃላቸው። ይህንን ደግሞ በዓለም ዋንጫ ደግሜ ታሪክ መስራት እፈልጋለው። ኢትዮጵያዊ ብሆንም ሰፋ ስናደርገው አፍሪካዊ ነኝ። ስለዚህ ለዓለም ዋንጫ ፈጣሪ ፈቅዶ ብንሳተፍ በጣም ደስ ይለኛል። በታንዛኒያው ጨዋታ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ስጫወት ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ተጫውተን ውጤት ይዘን ለመውጣት እንሞክራለን።