ከወሳኙ ጨዋታ በፊት ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን አከናውኗል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከታንዛንያ ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን ሠርቷል።

ከሜዳው ውጭ በታንዛንያ አንድ ለምንም የተሸነፈበትን ውጤት ቀልብሶ ለመጨረሻው አምስተኛ የማጣርያ ምዕራፍ ለማለፍ ነገ ወሳኝ ጨዋታውን የሚያደርገው ብሔራዊ ቡድኑ ከታንዛንያ መልስ በወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ጨዋታውን በሚያደርግበት አበበ ቢቂላ ስታዲየም ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቶ በዛሬው ዕለት ቦሌ በሚገኘው በቅዱስ ጊዮርጊስ ሜዳ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል።የዛሬው ልምምድ የመጨረሻ እንደመሆኑ መጠን ቀለል ያለ ኳስን መሠረት ያደረጉ እንቅስቃሴያቸው ሲከውኑ ተመልክተናል።

ባለፈው ማክሰኞ በጡንቻ መሳሳብ ምክንያት ልምምዷን አቋርጣ የወጣችው አንበሏ ናርዶስ ጌትነት በትናትናው ልምምድ በህክምና ምክንያት ያልተሳተፈች ቢሆንም በዛሬው ዕለት ለብቻዋ ተነጥላ ቀለል ያሉ ልምምዶችን ሰርታለች። ሆኖም ግን ለነገ ጨዋታ የመድረሷ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን ልምምዱ እንደተጠናቀቀ አሰልጣኝ ፍሬው እና የግብጠባቂው አሰልጣኝ ፀጋዘአብ በጋራ በመሆን ፊዞትራፒስት ይስሀቅ ሽፈራው ጋር በመደውል የናርዶስን የጤንነት ሁኔታ ያለበትን ደረጃ ሲጠይቁ አይተናል። በአጠቃላይ የናርዶስ የመሰለፍ አለመሰለፍ ጉዳይ ነገ የሚወሰን ይሆናል።ለ50 ደቂቃ በቆየው የዛሬው የመጨረሻ ልምምድ ከተጠናቀቀ በኃላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማህበር ያዘጋጁት የመልካም ምኞት የኬክ ቆረሳ የተካሄደ ሲሆን ማህበሩ በተወካዩ ምንያህል አማካኝነት አነቃቂ መልዕክት አስተላልፈዋል። በምላሹም ብሔራዊ ቡድኑን በመወከል አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለ ገብርኤል ስለተደረገላቸው ነገር ሁሉ አመስግነዋል።በሌላ ዜና የታንዛንያ ብሔራዊ ቡድን ትናት አመሻሽ ላይ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ከሰዓታት በኋላ ጨዋታውን በሚያከናውንበት አበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዱን የሚሰራ ይሆናል።

የነገ 10:00 ጨዋታን ከቡሩንዲ የመጡ አራት ዳኞች የሚመሩት ሲሆን የጨዋታ ኮሚሽነር ከሱዳን መሆናቸው ታውቋል።