ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ነገ ምሽት የሚከናወነውን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንደሚከተለው አንስተናል።

በድሬዳዋ ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ የተቃረነ ውጤት የገጠማቸው የባህር ዳር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። ምንም እንኳን ውድድሩ ሲጀምር ሁለቱ ቡድኖች በፉክክሩ ውስጥ ግምት ከተሰጣቸው ክልቦች ውስጥ ቢካተቱም አሁን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከነገ ተጋጣሚው በስድስት ነጥቦች ርቆ ሊጉን እየመራ ሲገኝ ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶችን ለማስተናገድ የተገደደው ባህር ዳር ከተማ በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ ተቀምጧል። የነገው ፍልሚያም ባህር ዳርን እንዲገኝ ወደሚጠበቅበት የፉክክር ደረጃ የሚያስጠጋ ቅዱስ ጊዮርጊስን ደግሞ በመሪነቱ እንዲገፋ በር የሚከፍት በመሆኑ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግ ይታመናል።

ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አንፃር ባህር ዳር ከተማ ከኳስ ጋር የመቆየት አዝማሚያ ሲታይበት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ወደ ቀደመ የመልሶ ማጥቃት አቀራረቡ እየተመለሰ ይገኛል። በደፈናው ስንመለከተውም ባህር ዳር በቅርብ ጨዋታዎች የፈጣን መልሶ ማጥቃት ሰለባ የሆነባቸው አጋጣሚዎች መበራከት ለቅዱስ ጊዮርጊስ መልካም አጋጣሚ ነው። በመጨረሻው የሲዳማ ቡና ጨዋታ እንኳን ከመምራት ተነስተው ሲሸነፉ የጣና ሞገዶቹ የኋላ ክፍል ከበስተ ጀርባው የሚተወው ቦታ ለጥቃት ኢላማ ሲሆን ተመልክተናል። ከዚህ አንፃር ባህር ዳሮች የኳስ ፍሰታቸው በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ቢቋረጥበት ቅፅበት የመከላከል ቅርፃቸውን ከመያዛቸው በፊት የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በብዙው ሊያስቡበት የሚገባ ዓይነት ነው። በእርግጥ በአራት ጨዋታዎች መረቡ ያልተደፈረው ቅዱስ ጊዮርጊስን በባህር ዳሮች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመያዝ ብቻ ሰብረው መግባት ቀላል የሚሆንላቸው አይመስልም።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዚህ ጨዋታ በፊት በስነ ልቦና ጥንካሬ ከፍታ ላይ እንዲገኝ የሚያደርጉት ብዙ ነገሮች አሉ። ያለሽንፈት 11ኛው ሳምንት መድረሱ ፣ ሊጉን መምራት መጀመሩ ፣ ከባድ የነበረውን የፋሲልን ጨዋታ በሰፊ ግብ ማሸነፉ እንዲሁም ግብ ካስተናገደ መሰነባበቱ በዚህ ረገድ የሚነሱ ነጥቦች ናቸው። ከዚህ ቀደም ሀዋሳ ከተማን ሲረቱ የነበራቸውን ብቃት በቀጣዩ የአዳማ ጨዋታ መድገም ሲሳናቸው ቢታይም አሁን ላይ ግን ቡድኑ አሸንፎ በመውጣት የወጥነት መስመሩን ያገኘ ይመስላል። ውጤት ከማሳካት ባለፈ ከኳስ ውጪ በቀላሉ ክፍተት የማይሰጥ አደረጃጀትን በመከተል ወደ ሳጥን አጥብቦ የመግባት ብቃት ባላቸው እንደአቤል ያለው ዓይነት ተጫዋቾቹን የሚጠቀምበት መንገድ አስፈሪነቱን አላብሶታል። ከተጋጣሚው ባህሪም አንፃር ይህ አካሄድ ነገም ሊደገም የሚችልበት አጋጣሚ አለ።

በእርግጥ ባህር ዳር ከተማ ከወላይታ ድቻ ጋር የነበረውን ጨዋታ ጨምሮ በውስን አጋጣሚዎች እንደፍፁም ዓለሙ እና ኦሴይ ማዉሊ አይነት ተጫዋቾቹን ለፈጣን ሽግግር ማሳለጫነት በማዋል የዓሊ ሱለይማንን ፍጥነት ያማከለ የመልሶ ማጥቃት መንገድን ያሳየበት አጋጣሚ አለ። ነገ ይህ ከሆነ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋሲሉ ጨዋታ የተለየ አቀራረብ ከገጠመው ከኳስ ጋር ብዙ ደቂቃ በማሳለፍ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር አቅሙ መፈቱኑ አይቀርም።

ይህንን ጨዋታ አሸብር ሰቦቃ በዋማ ዳኝነት ለመምራት ሲመደቡነት ክንፈ ይልማ እና ሻረው ጌታቸው ረዳት ሄኖክ አክሊሉ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ይሆናሉ።


የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ በድኖች እስካሁን በሊጉ ለአራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ ሁለት ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸው በአንድ ጨዋታ ያለግብ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ሁለቱም ሁለት ሁለት ጎሎችን ከመረብ አገናኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ባህር ዳር ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)

አበበከር ኑሪ

መሳይ አገኘሁ – ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ – ግርማ ዲሳሳ

በረከት ጥጋቡ

አብዱልከሪም ንኪማ – አለልኝ አዘነ

ፍፁም ዓለሙ

ዓሊ ሱሌይማን – ተመስገን ደረሰ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ቻርለስ ሉክዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሔኖክ አዱኛ

ያብስራ ተስፋዬ – ጋቶች ፓኖም

አቤል ያለው – ከነዓን ማርክነህ – አማኑኤል ገብረሚካኤል

እስማኤል አውሮ-አጎሮ