​ቅድመ ዳሰሳ | ሀዲያ ሆሳዕና ከ ጅማ አባጅፋር

የ11ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታን በሚከተለው መልኩ ዳሰነዋል።

ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ከሊጉ መሪ ደግሞ በሰባት ነጥቦች ርቀው 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ10ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ሁለት ጊዜ እየመሩ አቻ የሆኑበትን እና ባለቀ ሰዓት ሁለት ነጥብ እንዲጥሉ የተገደዱበትን ጨዋታ በቁጭት እያሰላሰሉ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ነገ ከጅማ ጋር ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከወልቂጤ ጋር ሲጫወቱ በብዙ መስፈርቶች የተሻሉ የነበሩት ሀዲያዎች በሁለተኛው አጋማሽ ያሳዩት የወረደ ብቃት ዋጋ አስከፍሏቸዋል። እስካሁን ካደረጋቸው 10 ጨዋታዎች ብዙ (7) ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች (በስምንተኛ ሳምንት ድሬዳዋን ሲገጥሙ ከተመዘገበው ጋር እኩል) ያደረገበትን ዕለት ያሳለፈው ቡድኑ የጨዋታ ደቂቃን አመጣጥኖ ከመጫወት፣ የተጋጣሚን እንቅስቃሴ ካለማንበብ እና ከትኩረት ማነስ ከመነጩ ምክንያቶች ሦስት ነጥብ አሳልፎ ባይሰጥ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ያደረገው እንቅስቃሴ ድንቅ ነበር። እንደ ወትሮ ኳስን ከመቆጣጠር ባለፈም ሁለቱን የመስመር ተመላላሾች (Wing backs) ሜዳውን ለጥጠው እንዲጫወቱ እና የሜዳው የመሐል ክፍል ላይ የቁጥር ብልጫ እንዲገኝ እንዲያስችሉ በማድረግ ሲጫወቱ የነበረበት መንገድ ጥሩ ነበር። ነገም ይህንኑ አዎንታዊ ጎን በማስቀጠል አንገቱን ቀና ያደረገውን ጅማን ለማሸነፍ እንደሚጥሩ ይታሰባል።

ከላይ እንደጠቀስነው የአሠልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ቡድን ባለቀ ሰዓት ሦስት ነጥብ ቢያጣም ከማጥቃት ወደ መከላከል ባሉ ሽግግሮች ላይ የሚወስደው ጊዜ መርዘሙ በፈጣን እና በረጅም ኳሶች እንዲጠቃ ያደረገው ይመስላል። በተለይ ደግሞ ሁለቱ የመስመር ተመላላሾች በእንቅስቃሴ እየተሳቡ ወደ ፊት የሚሄዱበት መንገድ ላይ ሚዛናዊነት አለመኖሩ ቡድኑ በዚህ ረደግ እንዲጋለጥ እንዳደረገው ይታመናል። የነገ ተጋጣሚው ጅማ ደግሞ አጥቂዎቹ ፈጣን መሆናቸው ሲታሰብ ይባስ ተጋላጭ እንዳይሆን ያሰጋል። ከዚህ በተጨማሪም እስካሁን በሊጉ ባገባው ልክ የተቆጠረበት ቡድኑ ያገኘውን ብልጫ አስጠብቆ የመውጣት እና ከተጋጣሚ የሚመጣ ጫናን የማጥፋት ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ወደ ሜዳ መግባት የግድ ይለዋል።

ከሊጉ ጅማሮ አንስቶ በወራጅ ቀጠናው ሲዳክር የነበረው እና ከ810 ደቂቃዎች ጥበቃ በኋላ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ ያገኘው ጅማ አባጅፋር የመዲናው ክለብ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ያሳየውን የተሻለ ብቃት በመድገም ዳግም ሌላ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ነገ ከሀዲያ ሆሳዕና የሚጠብቀውን ጠንካራ ፈተና ማለፍ የግድ ይለዋል።

ያለ ድል ያለፉትን ዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት ያሳለፈው ጅማ አባጅፋር በርካታ የተጫዋቾች ምርጫን እና የተጫዋች አደራደር ቅርፅን ከተጠቀመ በኋላ የማሸነፍን ሚስጢር በዳዊት እስቲፋኖስ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል ታግዞም ቢሆን አግኝቷል። የሊጉ ዝቅተኛው ግብ አስቆጣሪ እና ከፍተኛው ብዙ ግብ አስተናጋጅ ቡድን የሆነው ጅማ ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በአንፃራዊነት የኋላ መስመሩን ያሻሻለ ቢመስልም ጎል ፊት ያለው ብቃቱ ግን አሁንም ማሳደግ ይገባዋል። ከምንም በላይ ግን በአራት ጨዋታዎች ከሁለት ጎሎ በላይ ያስተናገደው የኋላ መስመር እንደተባለው ያለፉትን ጨዋታዎች መጠነኛ መሻሻል ያሳየ ሲሆን አዲስ አበባን ድል ባደረጉበት ጨዋታ ደግሞ ይበልጥ ጥሩ ሆኖ ነበር። በቡድናዊ መዋቅርም ሆነ በግል የሚሰነዘሩ የዐየር እና የመሬት ላይ ኳሶችን በማምከኑ ረገድም የተዋጣለት ጊዜ አሳልፈው ለሁለተኛ ጊዜ (በሰባተኛ ሳምንት ከአርባምንጭ ጋር) ግባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል። ከዚህ ውጪ የቡድኑ ልምድ ያላቸው አማካዮች የሆኑት ዳዊት እና መስዑድ የጨዋታውን ሂደት በማፍጠን እና በማቀዝቀዝ ረገድ ድንቅ ጊዜን አሳልፈው ስለነበር ነገም ብቃታቸውን ቡድኑ የሚሻ ይሆናል።

የጅማ የነገው ተጋጣሚ ካሉት ጠንካራ ጎኖች መካከል አንደኛው ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት ነው። በተለይ በመሐል ሜዳው ላይ የቁጥር ብልጫ በመውሰድ ተጋጣሚን ከኳስ ውጪ በማድከም ፈጣን የማጥቃት አጨዋወት መከተል ባህሪው ነው። ይህንን የቡድኑን አዎንታዊ ጎን ማምከኛ ዘዴ ደግሞ በጅማ በኩል የሚጠበቅ ሲሆን ከመቼውም በላይ በታታሪነት የመጫወቻ ሜዳዎችን መንፈግ እንደሚገባቸው ይገመታል። በተጨማሪም በጨዋታ 0.3 ግቦችን ብቻ እያስቆጠረ ያለው ቡድንም ፊት ላይ ስል መሆን እንደሚጠበቅበት ይታመናል። በተለይ ደግሞ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾቹ የሚያገኟቸውን የግብ ማግባት ዕድሎች መጠቀም እንደሚገባቸው ይታመናል።

በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ፍሬዘር ካሳ በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት ኤፍሬም ዘካሪያስ፣ መላኩ ወልዴ እና አስቻለው ግርማ ደግሞ በቤተሰብ ጉዳይ ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው፡፡ ጅማ አባጅፋር በበኩሉ ከአዲስ አበባ ሦስት ነጥብ ሲሸምት በ28ኛው ደቂቃ ተጎድቶ ከሜዳ የወጣውን አማካይ ሙሴ ከበላን በነገው ጨዋታም አያገኝም።

ይህንን ጨዋታ ሚካኤል ጣዕመ በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት ተመስገን ሳሙኤል እና ካሳሁን ፍፁም ረዳት ዳኞች እንዲሁም ኤፍሬም ደበሌ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ተመድቧል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት ታሪካቸው ከሁለት አይዘልም። ዓምናም ሁለት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለቱንም ጨዋታዎች ሀዲያ ሆሳዕና (1-0 እና 3-0) ማሸነፍ ችሏል።

ግምታዊ አሠላለፍ

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳ

ቃለዓብ ውብሸት – እሸቱ ግርማ – ሄኖክ አርፊጮ

ብርሃኑ በቀለ – ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን – ኢያሱ ታምሩ

ባዬ ገዛኸኝ – ሀብታሙ ታደሰ

ጅማ አባጅፋር (4-2-3-1)

አላዛር ማርቆስ

ወንድማገኝ ማርቆስ – ተስፋዬ መላኩ – የአብስራ ሙሉጌታ – ሽመልስ ተገኝ

መስዑድ መሐመድ – አልሳሪ አልመሐዲ

ዱላ ሙላቱ – ዳዊት እስጢፋኖስ – መሐመድኑር ናስር

ዳዊት ፍቃዱ