ኢትዮጵያዊያን ዕንስት ዳኞች የኦሊምፒክ የማጣሪያ ጨዋታን ይመራሉ

አራት ሴት ኢትዮጵያዊያን ዓለምአቀፍ ዳኞች በነገው ዕለት ጋቦሮኒ ላይ ቦትስዋና እና ታንዛኒያ የሚያደርጉትን የኦሊምፒክ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታን በዳኝነት ይመራሉ።

የ2024 ኦሎምፒክ በፈረንሳይ አስተናጋጅነት ፓሪስ ላይ ይደረጋል። በዚህ መድረክ ላይ ለመሳተፍ በእግርኳሱ በሴት ብሔራዊ ቡድናችን አማካኝነት ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራትም በማጣሪያው እየተካፈሉ ይገኛሉ። የአፍሪካ ዞን የማጣሪያ ጨዋታዎችን እየተደረጉ የሚገኝ ሲሆን የመልስ ጨዋታዎችም ከነገ ጀምሮ መደረጋቸውን ይቀጥላሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር ለከሚያከናውነው የመልስ ጨዋታ በተጨማሪ ሀገራችን በአራት ኢትዮጵያውያን ዕንስት ዳኞች ትወከላለች። ቦትስዋና ጋቦሮኒ ላይ በመጀመሪያው ማጣሪያ ከሜዳ ውጪ በታንዛኒያ 2ለ0 የተረታችው ቦትስዋና የመልስ መርሀግብሯን ነገ ማክሰኞ ምሽት 1 ሰዓት በሜዳዋ ስታከናውን እነኚህ አራት የሀገራችን ዳኞች ጨዋታውን እንዲመሩ ስለመመረጣቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ይህን ጨዋታ በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሲሳይ ራያ ስትመራው ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞቹ ወይንሸት አበራ እና ብርቱካን ማሞ በዳትነት ፣ አራተኛ በመሆን ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ፀሀይነሽ አበበ በጋራ እንዲመሩት በመመረጣቸው ወደ ስፍራው አምርተዋል።