አራት ክለቦች የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ በኢትዮጵያ ቡና ፣ ወልቂጤ ከተማ ፣ አዳማ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ላይ ጠንከር ያሉ ቅጣቶችን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ በአራተኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ በታዩ የዲሲፕሊን ጥሰቶች ዙሪያ ካደረገው ውይይት በኋላ በአራት የተለያዩ ክለቦች ላይ የቅጣት በትሩን ሰንዝሯል።

ወልቂጤ ከተማ በባህር ዳር ከተማ ሽንፈት ባስተናገደበት ወቅት ሀድያ ሆሳዕና በበኩሉ ከሀምበሪቾ ጋር ያለ ጎል ካጠናቀቀው ጨዋታ እና እንዲሁም አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ በተጋራው ጨዋታዎች ላይ የወልቂጤ ፣ የሀድያ እና የአዳማ ደጋፊዎች ጨዋታውን በመሩ ዳኞች ላይ አፀያፊ ስድብን ሰንዝረዋል በሚል አወዳዳሪው አካል ሦስቱም ክለቦች እያንዳንዳቸው የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ክፍያን እንዲፈፅሙ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

ኢትዮጵያ ቡና በፋሲል ከነማ 2-0 በተረታበት ጨዋታ የዕለቱ ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ እና ረዳቶቹ ላይ እንዲሁም ተጋጣሚ ቡድንን ጭምር የክለቡ ደጋፊዎች አፀያፊ ስድብን ስለመሳደባቸው እና የስታዲየሙን የወንበር ስብርባሪ ወደ ሜዳ መወርወራቸው ሪፖርት በመቅረቡ የክለቡ ደጋፊዎች ከዚህ በፊትም አፀያፊ ስድብ በመሳደባቸው ተቅጥተው ከነበረው ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው የ75 ሺህ የገንዘብ እንዲሁም ደግሞ ቁሳቁስ ወደ ሜዳ በመወርውራቸው 25 ሺህ ብር በድምሩ ክለቡ ብር 100 ሺህ እንዲከፍል ቅጣት ተወስኗል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቡና የቡድን መሪ እና የደጋፊ ማህበር ተወካይ የፕሪምየር ሊግ ውድድር እና ሥነስርዓት ኮሚቴ ለማነጋገር ጥሪም አስተላልፏል።