የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የአራተኛ ሣምንት ምርጥ 11

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሣምንት ጎልተው የወጡ ተጫዋቾችን መሠረት በማድረግ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አደራደር: 4-4-2

ግብ ጠባቂ

ፔፔ ሰይዶ – ባህርዳር ከተማ

ሴኔጋላዊው የጣና ሞገዶቹ የግብ ዘብ ፔፔ ሰይዶ ክለቡ ወልቂጤ ከተማ ላይ የ 3-0 ድል ሲቀዳጅ ቡድኑ ምንም ግብ እንዳይቆጠርበት ያደረገው አስተዋጽኦ የላቀ ነበር። በትክክለኛ የጊዜ አጠባበቅ ሲያቋርጣቸው ከነበሩት ኳሶች በተጨማሪ  የሳምሶን ጥላሁንን የፍጹም ቅጣት ምት ማዳንም ችሏል።

ተከላካዮች

ዓለምብርሃን ይግዛው – ፋሲል ከነማ

የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዓለምብርሃን ይግዛው ለቡድኑ በወሳኙ ጨዋታ ከፍተኛ የማጥቃት ተሳትፎን በታታሪነት ሲያግዝ ቆይቷል። ዓለምብርሃን የቡናማዎቹን የጥቃት ሂደት በማምከን በኩል ቡድኑ ስጋት እንዳይኖርበት ሲከላከል የተመለከትነው በመሆኑ የምርጥ ቡድናችን አካል ሆኗል።

በረከት ሳሙኤል – ሀዋሳ ከተማ

ምንም እንኳን ሀዋሳ ከተማ ያለጎል ጨዋታውን በማጠናቀቅ ድል ባይቀናውም ቡድኑ ጎል እንዳይስተናገድበት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። በተለይ በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች አጥቂዎችን በመቆጣጠር መልካም እንቅስቃሴ ያደረገው በረከት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቡድኑ ጫና ውስጥ በሆነበት ሁኔታ ከጉዳቱ ጋር እየተጋለ ኃላፊነቱን በሚገባ ሲወጣ ቆይቷል።

መናፍ ዐወል -ፋሲል ከነማ

ብዙ ትግል ይጠይቅ በነበረው ጨዋታ ቡድኑ አሸንፎ እንዲወጣ የኢትዮጵያ ቡና አጥቂዎችን በመቆጣጠሩ ረገድ መናፍ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። ከምኞት ደበበ ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠርም የዓየር ላይ ኳሶችን በመከላከል እና አደጋ የሚፈጥሩ ጥቃቶችን አቋርጦ በማራቅ ቡድኑ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ይዞ  እንዲወጣ ማድረግ ችሏል።

ደስታ ዮሐንስ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና የተጠበቀውን ያህል መልካም አጀማመር ባያደርግም ደስታ በየ ጨዋታዎቹ የግሉን ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው ደስታ ሻሸመኔን በረቱበት ጨዋታም በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ በኩል በሁለቱም ሚናዎች በልበ ሙሉነት ቡድኑን ያገዘ ሲሆን የመጀመርያውን ጎልም በፍፁም ቅጣት ምት በማስቆጠር ክለቡ የውድድር ዓመቱን የመጀመርያ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ሚናውን ተወጥቷል።

አማካዮች

ባሲሩ ዑማር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ጋናዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካይ ባሲሩ ክለቡ ድሬዳዋ ከተማ ላይ የ 3-2 ድል ሲቀዳጅ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ በቀላል እና የተሳኩ ቅብብሎቹ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ስኬታማ ቀን ሲያሳልፍ ከሳቢ እንቅስቃሴው ባሻገር የቡድኑን ሦስተኛ ግብም በስሙ ማስመዝገብ ችሏል።

ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን – ሲዳማ ቡና

አዲሱ የሲዳማ ፈራሚ ፍቅረኢየሱስ ቡድኑ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ሻሸመኔ ላይ ሲያሳካ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ውስጥ የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር። በርካታ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን በማድረግ የተጋጣሚን የግብ ክልል ከመፈተኑ ባሻገር ለቡድን አጋሮቹ ሲያቀብላቸው የነበሩት ስኬታማ ኳሶች በቦታው ተመራጭ አድርገውታል።

 

በረከት ደስታ – መቻል

የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ የሆነው በረከት ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም በሚታወቅበት ጥሩ አቋም ላይ ባይገኝም እራሱን ፈልጎ ለማግኘት እየታተረ ይገኛል። መቻል በፈታኙ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ሲረታ በረከት የማሸነፊያዋን ጎል በአስደናቂ ሁኔታ ከሳጥን ውጪ በማስቆጠር በቀጣይ ጨዋታዎች በራስ መተማመኑን ከፍ የሚያደርግለትን እንቅስቃሴ አስመልክቶናል።

አማኑኤል ገብረሚካኤል – ፋሲል ከነማ

ጉዳት በሚፈለገው ደረጃ አቅሙን አውጥቶ እንዳይጫወት ፈተና የሆነበት አማኑኤል ዳግም እየተወለደ መሆኑን በአራተኛው ሳምንት ያሳየውን ምርጥ እንቅስቃሴ መመልከት በቂ ነው። ቡድኑ በወሳኙ ጨዋታ ድል ያደረገበትን ሁለቱንም ጎሎች በማስቆጠር የነበረው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ በስብስባችን ውስጥ ሊካተት ችሏል።


አጥቂዎች

አዲስ ግደይ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በንግድ ባንክ ስኬታማ ጉዞ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው የመስመር አጥቂው አዲስ ቡድኑ ድሬዳዋ ላይ የ 3ለ2 ድል ባሳካበት ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ በጥሩ ሩጫ ሾልኮ በመውጣት ማስቆጠር ሲችል ባሲሩ ዑማር ላስቆጠራት የቡድኑ ሦስተኛ ግብም ቁልፍ መነሻ ነበር። ሆኖም ከውጤታማነቱ ባሻገር ሜዳ ላይ ሲያደርግ የነበረው ማራኪ እንቅስቃሴ በቦታው ተመራጭ አድርጎታል።

ሀብታሙ ታደሰ – ባህርዳር ከተማ

የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሐት-ትሪክ ሠሪ ሀብታሙ ታደሰ ቡድኑ ወልቂጤ ከተማን ሦስት ለምንም ሲረታ ሦስቱንም ግቦች በመጀመሪያው አጋማሽ በ 35 ደቂቃዎች ልዩነት ማስቆጠር ችሎ ከአቤል ያለው ጋር በተመሳሳይ አራት ግቦች የሊጉን ኮከብ ጎል አስቆጣሪነት በመምራት ላይ ይገኛል። አጥቂው ከእንቅስቃሴው ባሻገር ውጤታማነቱ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ ሆኗል።

አሰልጣኝ – ውበቱ አባተ

ዐፄዎቹ በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቡናማዎቹን በመርታት ተከታታይ ድል ሲያስመዘግቡ ለውጤቱ መገኘት አሰልጣኙ የመረጡት የጨዋታ መንገድ የሚደነቅ ነበር። ዐፄዎቹ ከሌሎች ጨዋታዎች በተሻለ በተደራጀ እንቅስቃሴ ለቡናማዎቹ ክፍት ቦታ በመንፈግ እና በፈጣን ሽግግር የተጋጣሚን ክፍት ቦታ በመጠቀም እጅግ ፈታኝ ሆነው መቅረብ ችለዋል። በዚህ ምክንያትም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ይህንን ምርጥ ቡድን እንዲመሩ ተመርጠዋል።


ተጠባባቂዎች

ናፍያን አልዌንዚ – መቻል
ያሬድ ባየህ – ባህርዳር ከተማ
ሱሌይማን ሐሚድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ጋቶች ፓኖም – ፋሲል ከነማ
ዓባይነህ ፌኖ – ባህርዳር ከተማ
አበባየሁ ዮሐንስ – ሲዳማ ቡና
ተገኑ ተሾመ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ዊልያም ሰለሞን – አዳማ ከተማ