ደሴ ከተማ በርካታ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

በከፍተኛ ሊጉ የሚሳተፈው ደሴ ከተማ  በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማስፈረም በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ደሴ ከተማ ለ2016 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በምድብ ለ የተመደበ ሲሆን በአሰልጣኝ ዳዊት ታደለ እየተመራ ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ ማድረግ ከጀመረ ሰንበት ብሏል። ለውድድሩም ይጠቅመኛል ያላቸውን ከፕሪሚየር ሊግ እና ከከፍተኛ ሊግ ወደ 16 የሚጠጉ ተጫዋቾችን የግሉ ማድረግ ችሏል ።

በዚህም የቀድሞው የኮልፌ ክ/ከተማ ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ እሸቱ ተሾመ ፤ ከዚህ ቀደም ለአውስኮድ ፣ ጅማ አባ ቡና እና ዳሞት ከተማ ሲጫወት የቆየው ግብ ጠባቂ ዘላለም ፀሐይ ፤ በተከላካይ ስፍራ ላይ ደግሞ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ቡራዩ ከተማ ቆይታ የነበረው ሚፍታህ ዐወል ፤ ለአዳማ ከተማ እና ነጌሌ አርሲ የተጫወተው ብሩክ ቦጋለ ፤ ከዚህ ቀደም ለሰበታ ፣ ለአዳማ እና ለኢትዮ ኤሌክትሪክ የተጫወተው ታፈሰ ሰረካ ፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣  በውሃ ሥራዎች ፣ መቻል ተስፋ እና ገላን ከተማ ቆይታ የነበረው ዘሪሁን አብይ እንዲሁም የቀድሞው የዲላ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ተጫዋች ዝናው ዘላለም ሆነዋል።

የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾችን ስንመለከት ከዚህ በፊት ለሀምበሪቾ ዱራሜ ፣ ነቀምት ከተማ እና ለጅማ አባጅፋር ሲያገለግል የቆየው ዋኩማ ዴንሳ ፤ የቀድሞው የአዳማ ተጫዋች አዲስ ግርማ ፤ ከዚህ በፊት በመቀለ 70 እንደርታ ፣ በለገጣፎ ለገዳዲ ፣ በሀምበሪቾ እና ገላን ከተማ ቆይታ የነበረው በሱፍቃድ ነጋሽ ፤ የቀድሞው የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ እና የኮልፌ ክ/ከተማ ተጫዋች ያሬድ ዓለማየሁ ፤ የቀድሞው የወላይታ ዲቻ ተጫዋች እንድሪስ ሰዒድ ናቸው።

በአጥቂ መስመር ላይ ከዚህ ቀደም ለወረኢሉ የተጫወተው በረከት ወሰን ፤ ከዚህ በፊት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተስፋው ቡድን እስከ ዋናው ቡድን ያገለገለው ፀጋ ደርቤ ፣ የቀድሞው የሀላባ ከተማ ተጫዋች አቡሽ ደርቤ ከዚህ በፊት ለቤንችማጂ ቡና ፣ ዳሞት ከተማ እና ቡራዩ ከተማ የተጫወተው ሙሉጌታ ካሳሁን ሆነዋል።