መረጃዎች| 19ኛ የጨዋታ ቀን

አምስተኛው ሳምንት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ተጠባቂ ጨዋታዎች ይቀጥላል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በዚህ ሳምንት ጠንካራ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ጨዋታዎች አንዱ የሆነው ተጠባቂው የሩዱዋ ደርቢ የነገው ቀዳሚ ፍልሚያ ይሆናል።

ከአራት ጨዋታዎች አንድ ድል እና ሦስት የአቻ ውጤቶች አስመዝግበው በስድስት ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኃይቆቹ ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች ወደ ድል ለመመለስ ሲዳማን ይገጥማሉ። ባለፉት ጨዋታዎች የተጫዋቾች ሚና እየቀያየሩ በአመዛኙ አጥቂዎቹ ላይ ባነጣጠሩ ተሻጋሪ ኳሶች ለማጥቃት የሞከሩት ኃይቆቹ የማጥቃት አቅማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀዛቀዘ መጥቷል። ቡድኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት መዳከም እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግቡን ያላስደፈረው ጠንካራ የተከላካይ ክፍል የገነቡት አሰልጣኝ ዘርዐይ ሙሉ በነገው ጨዋታ በ180 ደቂቃዎች ምንም ግን ያላስቆጠረውን ማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በመጨረሻው ጨዋታ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ጣፋጭ ድል የተቀዳጁት ሲዳማዎች ከነበረባቸው ከፍተኛ ጫና በመጠኑም ቢሆን እፎይ ብለዋል። ሲዳማዎች ከአራት ጨዋታዎች ሁለት ሽንፈት በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ የአቻና ድል ውጤቶች አስመዝግበዋል። የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን በጨዋታዎቹ ምንም እንኳን ሽንፈቶች ቢያስተናግድም በመከላከሉ ረገድ ግን በአንፃራዊነት ጥሩ ጎኖች ነበሩት። በሦስት ጨዋታዎችም ሦስት ግቦች ነበር የተቆጠሩበት።

ሆኖም ቡድኑ በጨዋታዎች ከፍተኛ የሆነ የግብ ድርቅ ውስጥ ነበር በተጠቀሱት ጨዋታዎችም አንድ ግብ ብቻ ነበር ያስቆጥረው። በመጨረሻው ሳምንት ላይ ግን ምንም እንኳ በተጋጣሚው ከባድ ፈተና ባይገጥመውም ግቦች ወደ ማስቆጠር ተመልሷል። ይህም በጫና ውስጥ ለነበረው ቡድን ጥሩ የሥነ-ልቦና ስንቅ ነው። በነገው ጨዋታ ላይ ግን በሦስት ጨዋታዎች ምንም ግብ ያላቆጠረ ጠጣር የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን እንደ መግጠማቸው ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም። አሰልጣኝ ስዩም ከበደም ወደ ግብ ማስቆጠር የተመለሰውን ቡድናቸው ጥንካሬውን የማስቀጠል የቤት ሥራ ይጠብቃቸዋል።

ሲዳማ ቡና ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ያሉት ይገዙ ቦጋለ እና ፊሊፕ አጃህን በነገው ጨዋታም አያገኝም ። በተጨማሪም አበባየሁ ዮሐንስ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ ያልፈዋል። ሀዋሳዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በ26 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ሲዳማ ቡና አስር ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ በድምሩ 57 ኳሶች መረብ ላይ ሲያርፉ ሲዳማ 31 ሀዋሳ ደግሞ 26 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሐል ዳኝነት ሲመራው ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ኢንተርናሽኛል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በረዳት ዳኝነት ተመድበዋል፤ ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በበኩሉ አራተኛ በመሆን ለጨዋታው ተሰይሟል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ የሆነውና ሁለት የመዲናይቱን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ምሽት 12:00 ሲል ይጀምራል።

በመጀመርያው ሳምንት ላይ ባህር ዳርን ካሸነፉ በኋላ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቁት መድኖች ከአራት ጨዋታ አንድ ድል፣ ሁለት አቻና አንድ ሽንፈት አስመዝግበው አምስት ነጥቦች ሰብስበዋል። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው ጨዋታዎች በአብዛኛው በፈጣን በሽግግሮች ላይ የተመረኮዘ አጨዋወት ነበረው። ሆኖም የአጨዋወቱ ውጤታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። በተለይም የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ብዙ ክፍተቶች ተስተውሎባቸዋል። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩም የማጥቃት አጨዋወቱ መዳከም ያሳያል። በመጨረሻው የሊግ ጨዋታ ውስን የአጨዋወት ለውጥ ያደረጉት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በነገው ወሳኝ ጨዋታ በዋነኝነት የግብ ማስቆጠር ችግራቸው መላ ከማበጀት ባለፈ የነገው ተጋጣምያቸው የሊጉ ከፍተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረ ቡድን እንደመሆኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ አስተናግዶ መሻሻሎች ያሳየው የተከላካይ ክፍላቸው ጥንካሬ ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።

ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሦስት ድልና አንድ የአቻ ውጤት አስመዝግበው በሊጉ አናት ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን መልሰው ለማግኘትና ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ወደዚህ ጨዋታ ይገባሉ። መስመሮቹን ይበልጥ የማጥቅያ መንገዳቸውን አድርገው ጠንካራ የፊት መስመር የገነቡት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በጨዋታ በአማካይ 2.7 ግቦች የሚያስቆጥር አይምሬ የፊት መስመር ገንብተዋል። የማጥቃት አጨዋወታቸውም የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነው። ሆኖም ቡድኑ በሁለት ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን የሚሰጡ አማካዮች እንደመጫወቱ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አለው ለማለት አያስደፍርም። በአራት ጨዋታዎች የተቆጠሩባቸው የግብ መጠን ስድስት መሆኑም የዚ ማሳያ ነው። ይህም ከሌሎች ሁለት ክለቦች በጋራ በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስተናገደ ቡድን ያደርገዋል። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታም የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት ላይ ውስን ለውጦች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ቀላል ልምምድ ከጀመረውና ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ ወደ ሜዳ ይመለሳል ተብሎ ከሚጠበቀው ቢንያም በላይ ውጭ ጨዋታውን የሚያመልጠው ተጫዋች የለም። በመድን በኩል አዲስ ተስፋዬ ከጉዳት ሲመለስ ሀቢብ ከማል፣ በርናንድ ኦቼንግ እና ተካልኝ ደጀኔ በጉዳት አይሰለፉም። የአብዱልከሪም መሐመድ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ 25 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ ሲኖራቸው 18 ጊዜ ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ 47 ጎሎች ፣ 2 ጊዜ ያሸነፈው መድን ደግሞ 14 ግቦችን አስቆጥረው አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።

ይህንን ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት ይመራዋል፤ በረዳት ዳኝነት ደግሞ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና አሸብር ታፈሰ ፣ አራተኛ ዳኛ በመሆን ደግሞ ኤፍሬም ደበሌ ተመድቧል።