የኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዩጋንዳ ይሳተፋል

ከቀናት በኋላ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴካፋ ዋንጫ የኢትዮጵያ ከ15 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተሳታፊ መሆኑ ታውቋል።

በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ከአራት ዓመት በፊት በኤርትራ አስተናጋጅነት የተካሄደው የሴካፋ ከ15 ዓመት በታች የወንዶች ብሔራዊ ቡድን ውድድር ዘንድሮ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከፊታችን ቅዳሜ ጥቅምት 24 ጀምሮ በስምንት ሀገሮች መካከል መካሄድ ይጀምራል። የመጀመርያውን ውድድር ያስተናገደችው ኤርትራ እና ሱዳን ከውድድሩ ውጭ ከመሆናቸው በቀር ኢትዮጵያን ብሩንዲ ፣ ኬንያ ፣ ሶማሊያ ፣ ታንዛንያ ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ሩዋንዳ እንዲሁም ዛንዚባር እና ጁቡቲ አዲስ ተሳታፊ ሀገራት በመሆን ይካፈላሉ።

ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ስለመሆኑ በይፋ ባይገለፅም ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ስሪ ፖይንት አካዳሚ ከፓይለት ፕሮጀክት ውድድር ጥቂት ተጫዋቾችን በማካተት ሀገርን ወክሎ በውድድሩ እንደሚሳተፍ ታውቋል። በእንግሊዛዊው ዋና አሰልጣኝ ሙሳ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ዕለት ከ27 በላይ የልዑካን ቡድን በመያዝ በሁለት ተከፍሎ ወደ ስፍራው እንደሚያቀና ይጠበቃል። ኢትዮጵያ በምድብ ሀ ከዩጋንዳ ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጁቡቲ ጋር ስትደለደል የመጀመርያ ጨዋታዋን የፊታችን ቅዳሜ ከደቡብ ሱዳን ጋር የምታደርግ ይሆናል።