የአሰልጣኞች አስተያየት | አዳማ ከተማ 0-0 ኢትዮጵያ ቡና

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና ያለ ጎል ካጠናቀቁት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ቡድናቸው ስለማድረጉ

“ዛሬ እንደ ቡድን ጥሩ አልነበርንም ፤ ጥሩም አልተጫወትንም። በተለይ የምናገኛቸውን ኳሶች ቶሎ ቶሎ እናበላሽ ነበር እና ለዚህ ነው የጎል ዕድል መፍጠር ያልቻልነው፡፡ በመጀመሪያው አርባ አምስት ትልልቅ ቦታዎችን አግኝተናል ግን መጠቀም ስላልቻልን ጎል ማግባት አልቻልንም ፤ የጎል ዕድልም መፍጠር አልቻልንም፡፡

ስለ ውጤቱ ተገቢነት

“አዎ ሜዳ ላይ ከነበረን አቋም አንፃር አንድ ነጥብ ማግኘት መጥፎ አይደለም፡፡

ውጤት አለመያዙ ከተጋጣሚ ወይንስ ከቡድኑ ድክመት

“መጀመሪያም ተናግሪያለሁ። ቡና ጠንካራ ቡድን ነው። ግን በምፈልገው መጠን ተጫውተናል ብዬ አላስብም አንዳንድ ተጫዋቾች ሜዳ ላይ ጥሩ አልነበሩም ይሄ ደግሞ ያጋጥማል ይሄንን አርመን በሚቀጥለው ጨወታ ራሳችንን እናዘጋጃለን፡፡”

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለ ጨወታው

“ጥሩ ነው። የጨዋታው ሂደት ያው ሁል ጊዜ ስንጫወተው የምንገምታቸው ነገሮች አሉ። እንደተለመደው ተጋጣሚ ከእኛ ኋላ ያለውን ቦታ መጠቀም ነው የሚፈልገው። ስለዚህ እነሱ ሜዳ ላይ ቁጥሩ የተከማቸ ተጫዋች ስለላ መፍትሄው ምንድነው የሚለውን እዛ ላይ መስራት ነው ፤ የተለመዱም ነገሮች ናቸው። ባለፈውም አሁንም ባለው ጨዋታ ከእንቅስቃሴ አንፃር የተከፈቱ መንገዶች ነበሩ። ያንን ለመጠቀም ነበር ጥረት ስናደርግ የነበረው፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ እና በሁለተኛው አጋማሽ ስለነበረው ሁለት ዓይነት መልክ

“ለውጥ ለማድረግ ያሰብነው የመጀመሪያው አርባ አምስት ደቂቃ ላይ ወደ እነርሱ ሜዳ እየተጠጋን በመጣን ቁጥር የእነርሱን ኋላ መስመር ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያጠቡና መስመሩን ነው የሚከፍቱት። ይሄን ክፍት ቦታ ደግሞ በአግባቡ አልተጠቀምንም። ስለዚህ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ እና እየገፋን የምናስወጣቸው ከሆነ መጨረሻ ላይ ራሳቸውን ስለሚያጠቀሙ ያንን ክፍት ቦታ ለመጠቀም ነበር ዕረፍት ላይ ለማስተካከል የሞከርነው፡፡

ስለ ደስተኝነታቸው

“አዎ ጥሩ ነው ያለው ነገር ጥሩ ነው፡፡ምክንያቱም አንድ የሆነ ነገር ከማድረግ አንፃር ነው ጥረት እያደረግን ያለነው ስለዚህ በዛ ውስጥ መቆየታችን በራሱ ጥሩ ነው፡፡ ከውጤት አንፃር ሲለካ በተወሰነ ደረጃ ወደ ኋላ የቀረንበት ነው ፤ ይሄንን ማሻሻል ይኖርብናል፡፡