ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ከሽንፈት ያገገመበትን ድል አስመዝግቧል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

ፋሲል ከነማዎች ከቆሙ ኳሶች መነሻ ባደረጉ ሦስት ግቦች ሰበታ ከተማን በመርታት ከቅዱስ ጊዮርጊሱ አስደንጋጭ ሽንፈት ያገገሙበትን ወሳኝ ሦስት ነጥብ አስመዝግበዋል።

ፋሲል ከነማ ከጊዮርጊሱ ሽንፈት ባደረጋቸው ለውጦች ሰዒድ ሁሴንን በዓለምብርሀን ይግዛው ፣ ከድር ከሊባሊን ጉዳት በገጠመው በያሬድ ባየህ እንዲሁም ከስድስት ጨዋታ በኋላ የተመለሰው ሀብታሙ ተከስተን በበዛብህ መለዮ ቦታ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ አስገብቷል። ሰበታ ከተማዎችም ዓለማየሁ ሙለታ ፣ በረከት ሳሙኤልን እና አብዱልሀቪዝ ቶፊቅን በአዳማው ሽንፈት ተሰልፈው በነበሩት በኃይሉ ግርማ ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና አንተነህ ናደው ምትክ ተጠቅመዋል።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ሰበታ ከተማዎች በቅርቡ ህይወቱ ላለፈው እና በከፍተኛ ሊግ በተለያዩ ክለቦች ተጫውቶ ያለፈው የቀድሞው ተጫዋቻቸው ታምራት ባልቻን የሚዘክር ባነር ይዘው የማስታወሻ ፎቶ ተነስተዋል።


ሰባት ተፈጥሮአዊ የተከላካይ መስመር ተሰላፊዎች በመጀመሪያ ተሰላፊነት ያስጀመሩት ሰበታ ከተማዎች በመከላከሉ ረገድ ፍፁም የተዋጣለት የመጀመሪያ አጋማሽ አሳልፈዋል። ፋሲል ከነማዎች በመስመር ሆነ መሀል ለመሀል የሚደረጉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ተቸግረው በታዩበት በመጀመሪያው አጋማሽ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ከሚመቱ እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች ከሚነሱ ኳሶች ውጭ በክፍት ጨዋታ የጠሩ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ተስተውሏል።
ሰበታ ከተማዎች ከመከላከል ባለፈው በአዳማ እንደሸነፉበት ጨዋታ ሁሉ የተጋጣሚን የኳስ ቅብብሎች በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ለማቋረጥ ጥረቶችን ሲያደርጉ የተመለከተን ቢሆንም አንደ አዳማ ጨዋታ ሁሉ ከፍላጎት ባለፈ እምብዛም ውጤታማ አልነበሩም። ነገርግን የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ወቅት ሱራፌል ዳኛቸው ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ በረከት ደሰታ ሳይጠበቅ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑ እየመራ ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመሩ አስችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች የአቻነቷን ግብ ፍለጋ አጋማሹን የተሻለ ጫና በመፍጠር ነበር የጀመሩት ፤ ነገር ግን በተለይ በሚያጠቁበት ወቅት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት በቁጥር አናሳ መሆናቸውን ተከትሎ ማጥቃታቸው ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል።

በሰበታ በተወሰነ መልኩ ብልጫ የተወሰደባቸው ፋሲሎች በ60ኛው ደቂቃ ወደ ግራ ካደላ አቋቋም ፋሲሎች ያገኙትን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቢልክም የግቡ ቋሚን ለትማ የተመለሰችውን ኳስ ሰዒድ ሀሰን ወደ ግብነት በመቀየር ፋሲሎች በጨዋታው የበላይነት እንዲያስቀጥሉ አስችሏል።

ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ከፍ ባለ የራስ መተማመን ስሜት መጫወት የጀመሩት ፋሲሎች ተጨማሪ ግብ ሊያስቆጥሩበት የሚችሉበትን አጋጣሚ በ83ኛው ደቂቃ ላይ አለማየሁ መለታ ሽመክት ጉግሳ ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት አማካኝነት ቢያገኙም ኦኪኪ አፎላቢ ሳይጠቀምባት ቀርቷል።

በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች በኦኪኪ አፎላቢ እና በረከት ደስታ ለጎል ተቃርበው በነበሩት ፋሲሎች በኩል 87ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ሱራፌል ዳኛቸው ያሻማውን የማዕዘን ምት በረከት ደስታ በግንባሩ በመግጨት የቡድኑን ሦስተኛ ግብ አስቆጥሯል።

ፋሲል ከነማዎች ድላቸውን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 21 በማሳደግ በ2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ሰበታ ከተማዎች በ7 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።