በአብዩ አረጋሽ
በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ7ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች አዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ድል ሲቀናቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ እንዲሁም ባሕር ዳር ከተማ እና መቻል ነጥብ ተጋርተዋል

አዳማ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም 9:00 ላይ አዳማ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ አዳማ ከተማ 2ለ0 አሸንፏል። በመጀመሪያው አጋማሽ አዳማ ከተማ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቢሆንም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ሳያስቆጥሩ አጋማሹ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ በ54ኛው ደቂቃ በአቡበከር ሳኒ ላይ በተሠራ ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ቢንያም አይተን ወደ ግብነት በመቀየር አዳማን መሪ አድርጓል። በ84ኛው ደቂቃ ደግሞ ፍጹም አለሙ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የሀዋሳ ከተማው ቹኩቡውካ አንቶኒ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠሩ አዳማ ከተማ የመሪነቱን ልዩነት ወደ ሁለት አሳድጓል። በመጨረሻም ጨዋታው 2ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ
በአዲስ አበባ ስታዲየም 9:30 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወላይታ ድቻ የተገናኙ ሲሆን ጨዋታው ያለ ግብ 0 ለ 0 ተጠናቋል። ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኳስ ቁጥጥር የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያሳይም ወላይታ ድቻ በግብ ሙከራዎች የተሻለ ብቃት አሳይቷል። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ወላይታ ድቻ ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርግም ዕድሎቹን ወደ ግብነት መቀየር ተስኖት ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ባሕር ዳር ከተማ ከ መቻል
በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም 10:00 ላይ ባሕር ዳር ከተማ ከመቻል ያደረጉት ጨዋታም ያለ ግብ 0 ለ 0 ተጠናቋል። በመጀመሪያው አጋማሽ መቻል በኳስ ቁጥጥር የተሻለ ቢሆንም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አልተደረጉም። በሁለተኛው አጋማሽም ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በማድረግ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ኳስና መረብ ማገናኘት ሳይችሉ ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት 0 ለ 0 ተጠናቋል።
ነጌሌ አርሲ ከ ሲዳማ ቡና
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምሽት 12:00 ላይ ነጌሌ አርሲ ከሲዳማ ቡና የተገናኙ ሲሆን ሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና 2 ለ 0 በማሸነፍ ሶስት ነጥብ ወስዷል። ጥሩ ፉክክር በተደረገበት በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ግን ነጌሌ አርሲዎች ብልጫ መውሰድ ችለዋል። ሆኖም ጥቂት
የግብ ሙከራዎች የተደረጉበት የመጀመሪያው አጋማሹ ግብ ሳይቆጠር ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ነጌሌ አርሲ ጥሩ እንቅስቃሴ ቢያሳይም በ83ኛው ደቂቃ ብርሃኑ በቀለ በግሩም ሁኔታ ያቀበለውን ኳስ መስፍን ታፈሰ ወደ ግብነት በመቀየር ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጓል። በ89ኛው ደቂቃ አቤል ያለው ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር የሲዳማ ቡናን መሪነት ወደ 2 ለ 0 አሳድጓል።
በዚህም ሲዳማ ቡና የአምና ተፎካካሪውን ነጌሌ አርሲ በማሸነፍ በሊጉ ሰንጠረዥ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ነጌሌ አርሲ በበኩሉ በሉጉ አናት ላይ ያለውን ቦታ መያዙን ቀጥሏል።
በአጠቃላይ በ7ኛው ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች ሲዳማ ቡናና በአዳማ ከተማ ድል ሲቀናቸው የተቀሩት ሁለት ጨኣታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

