ሪፖርት | ፈረሠኞቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

በምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ መድንን 3-0 ረቷል።

በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ኢትዮጵያ መድን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲገናኙ መድን ከሀዋሳ አቻ ሲለያይ ከተጠቀመው አሰላለፍ አሚር ሙደሲር እና አቡበከር ወንድሙን አሳርፎ በያሬድ ዳርዛ እና ኦሊሴማ ቺኔዱ ሲተካ ከአዳማ ጋር አቻ በተለያዩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ደግሞ አማኑኤል ኤርቦ አርፎ በሞሰስ ኦዶ የተቀየረበት ብቸኛ ለውጣቸው ሆኗል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግበትም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ኢትዮጵያ መድኖች የተሻሉ ነበሩ። 10ኛው ደቂቃ ላይም ኦሊሴማ ቺኔዱ በግራ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ከብሩክ ሙሉጌታ ጋር ተቀባብሎ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግበትም በተከላካይ ተጨርፎ ፈታኝ የነበረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ  በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል።


በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት መድኖች በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ የፈረሠኞቹን ሳጥን መፈተናቸውን ቀጥለዋል። 20ኛው ደቂቃ ላይም ኦሊሴማ ቺኔዱ ከቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ሲመልበት የተመለሰውን ኳስ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በፍጥነት ማራቅ ችሏል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም መድኖች ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። ቹኩዌመካ ጎድሰን በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ወገኔ ገዛኸኝ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።


በአጋማሹ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ከነበሩበት የተቀዛቀዘ የጨዋታ ስሜት በመጋል በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 37ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አቤል ያለው ከዳዊት ተፈራ በተቀበለው ኳስ ተከላካይ አታልሎ ለማለፍ ሲሞክር የመስመር ተከላካዩ ያሬድ ካሳየ ጥፋት ሠርቶበታል በሚል በዋና ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ውሳኔ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ አቤል ያለው አስቆጥሮት ፈረሠኞቹን መሪ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ቀጥሎ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መድኖች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም ጠንካራውን የጊዮርጊስን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ጥሰው ለመግባት ተቸግረዋል። በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ በሚያገኙት ኳስ አልፎ አልፎ አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ፈረሠኞቹ በዚሁ እንቅስቃሴያቸው 57ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ሄኖክ አዱኛ አቤል ያለው አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ኳሱን ያገኘው ሞሰስ ኦዶ ዓየር ላይ እንዳለ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎታል።


በሁለት ግቦች ልዩነት ከተመሩ በኋላ ለጥቂት ደቂቃዎች የተቀዛቀዙት መድኖች በድጋሚ በማንሠራራት እና በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ግብ ለማስቆጠር መታተራቸውን ቢቀጥሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ደካማ ነበር ይባስ ብሎም 81ኛው ደቂቃ ላይ በሠሩት ስህተት ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። አቤል ያለው ተጭኖ በቀማው ኳስ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራን አታልሎ በማለፍ ተቀይሮ ለገባው አማኑኤል ኤርቦ  አመቻችቶ ሲያቀብል አማኑኤልም ያገኘውን ኳስ በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎታል።


በሦስት ደቂቃዎች ልዩነትም መድኖች ቀይረው ባስገቡት ሙሴ ከበላ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ተመልሶባቸዋል። ጨዋታውን በተረጋጋ ሁኔታ ያስቀጠሉት ፈረሠኞቹም በጭማሪ ደቂቃዎች በአላዛር ሳሙኤል እና አማኑኤል ኤርቦ ተጨማሪ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።