አሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 0-1 ሀዋሳ ከተማ

“ልጆቼ ጨዋታውን በምን መልኩ እንዳከበዱት ለእኔም ትንሽ ግራ ያጋባኝ ነገር ነው” አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ


“ይሄን ጨዋታ ማሸነፋችን ያለውን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ‘ሩዱዋ ደርቢ’ በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ሁለቱ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ አካፍለዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው…

“በእውነት ከጠበኩት በታች ነው እንደቡድንም እንደግልም ፤ ምናልባት ልጆቼ ጨዋታውን በምን መልኩ እንዳከበዱት ለእኔም ትንሽ ግራ ያጋባኝ ነገር ነው። እንደዚህ አልጠበኩም ፤ ከፋሲል ጀምሮ ጥሩ እንቅስቃሴ እና ዕድገት እያሳየን መጥተናል። ዛሬ ውጤት ይዘን እንወጣለን ብዬ ነበር ያሰብኩት ግን ሜዳ ላይ ያልጠበቅነው ነገር ነው የገጠመን። በተለያየ መንገድ ተጫዋቾች ለመቀየር ሞክረናል ግን ያ ደረጃ ሊመጣ አልቻለም። በውጤቱ በጣም ተከፍቻለሁ ፤ በዚህ አጋጣሚ የሲዳማ ደጋፊዎችን ከልብ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ።”

ጫና ውስጥ ስለመሆናቸው…

“የአሰልጣኝ ህይወት ይሄ ነው ፤ ጫናዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ይሄ የክለቡ ውሳኔ ነው። ስለዚህ የሚያሳስበኝ ነገር የለም። ክለቡ ከፈለገኝ እቀጥላለሁ ፤ ካልፈለገኝም ባጋጠመኝ ነገር አልፀፀትም። የምችለውን ያህል ሞክሪያለሁ ፤ ጥሪያለሁ።”

ስለማይክል ኪፖሩል የዕለቱ ብቃት…

“ማይክል ሁሉንም ተጫዋቾች ብትጠይቃቸው ልምምድ ላይ በጣም ጥሩ ነው። በጫና ውስጥ ሆኖ እየተጫወተ በምንፈልገው ልክ ልናገኛው አልቻልንም እንጂ ጥሩ ልጅ ነበር። ምናልባት ወደ ሁለተኛ ዙር ተጫዋቾች የመቀየር ሀሳብ ሊኖር ይችላል ቢሆንም ግን በሁሉም ነገር ደስተኛ አይደለሁም።”

በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ከነበራቸው ብቃት አንፃር ቡድናቸውን እንዳሰቡት ስለማግኘታቸው..

“አላገኘሁትም ! የአጥቂ ክፍላችን የሰላ ቢሆን ፤ ለምሳሌ ይገዙን እና አጃህን ብትወስድ አብዱርሀማን ራሱ ባይታመም ለሰላ የፊት መስመር የቀረቡ ነበሩ። በጎል ስትታጀብ ነው ሌላው የሚነቃቃው። ይሄ በግራ እና በቀኝ ያመሳሰልነው ደበዘዘብን እና ከፍተኛ ሥራ ይጠብቀናል።”

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው…

“ጨዋታው ጠንካራ ነበር። ምክንያቱም አንደኛ ደርቢ ነው ፤ ሁለተኛ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥተናል ወደ አሸናፊነት መምጣት ከእኛ ይጠበቃል። ለመሪዎቹ ቅርብ ሆኖ ወደ ዕረፍት ለማምራትም የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ የግድ ነበር። በመጀመሪያ 15 እና 20 ደቂቃ በጣም ተጭነን የጎል አጋጣሚዎችንም ፈጥረናል። የመረጋጋት ጉዳይ ሆኖ ማስቆጠር አልቻልንም። ከዕረፍት በኋላ ግን ያንን ነው የተነጋገርነው እና ኢዮብ ተረጋግቶ ባስቆጠረው ግብ አሸናፊ ሆነናል።”

ስለቡድኑ የእስካሁኑ ጉዞ…

“ቡድናችን እስካሁን ከዓምናው የሚለየው ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን ነው። ከግብ ጠባቂ ጀምረን ኳሱ እያደገ ነው የሚሄደው ያንን እንቅስቃሴ ከጨዋታ ጨዋታ እያየን ነው። ግን ሁል ጊዜ ነጥብ ስትጥል የሆነ ነገር ትቀንሳለህ እና መጀመሪያ ላይ ሁለቱ ጨዋታ ላይ የጣልናቸው ነጥቦች በራስ መተማመን እንዳንጫወት አድርገውናል። ይሄን ጨዋታ ማሸነፋችን ያለውን እንቅስቃሴ ለማስቀጠል ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው። ከጨዋታ ጨዋታ ያለን እንቅስቃሴ ጥሩ ነው።”

ስለ ቀጣዩ ዕረፍት ጊዜ…

“ተጠናክረን የምንሰራው ከዚህ በኋላ ነው። ብዙ ዕረፍት ለተጫዋቾቻችን አንሰጥም። ከዚህ በኋላ ያሉት ጨዋታዎች ጠንካራ ናቸው እና ዘንድሮ እያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ነጥብ መውሰድ በጣም ከባድ ነው። ስለዚህ በዛ ልክ በተለይ ወደፊት ስንሄድ የምናንሰውን በልምምድ ቡድናችንን አዘጋጅተን ከዕረፍቱ በኋላ ጠንካራውን ሀዋሳ ከተማ እናያለን ብዬ ነው የማስበው።”