የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ መድን 0-3 ቅዱስ ጊዮርጊስ

“እኛ በምንፈልገው መልኩ ለመጫወት ሞክረናል” አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ


“ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ሰጥተው ጥሩ ውጤት ይዘን ወጥተናል” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

የምሽቱ ጨዋታ በፈረሰኞቹ የበላይነት ከተቋጨ በኋላ ከአሰልጣኞች ጋር ቆይታ አድርገናል።

አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ – ኢትዮጵያ መድን

ስለጨዋታው…

“እኛ በምንፈልገው መልኩ ለመጫወት ሞክረናል። እስከመጨረሻው ጥረናል ፤ ጥሩ ነው መጥፎ ነገር የለውም። መጥፎ ነገሩ የተወሰኑ ስህተቶች ፤ ከፍፁም ቅጣት ምት በኋላ ጎል የተቆጠረብን ነው። ፍፁም ቅጣት ምቱ ፍትሀዊ ያልሆነ ነው። ግን ከዛ በኋላ ማሻሻል የምንችላቸው ነገሮች ነበሩ ፤ የግል ስህተቶች ተጨምረውበት ማለት ነው። ተከላካዮቻችን አካባቢ ያለመረጋጋት ነበር። እሱን በሂደት እያስተካከልን እንመጣለን። በመጪው ዕረፍት ተደጋጋሚ ጉዳት የገጠማቸው ልጆችም ይመለሳሉ ብለን እናስባለን። በርናንድ ፣ ሀቢብ ፣ ተከልኝ እና ሌሎቹም መምጣት ስለሚችሉ ጥሩ ነው። ግን የሄድንበት መንገድ ጥሩ ነበር። 3-0 ተሸንፈናል ፤ ሽንፈት ሽንፈት ነው። ተቀብለን ተሻሽለን ለመምጣት እንሞክራለን።

ፍፁም ቅጣት ምቱ ስለነበረው ተፅዕኖ…

“እውነት ነው ! በጣም የበላይነት ነበረን ፤ ግልፅ እኮ ነው። ግን ያው ከዛ በኋላ ማስተካከል የምንችልባቸው ሁኔታዎች ነበሩ። ከዛም በኋላ ማግባት እንደምንችል እርግጠኛ ነበርኩ። የሳትናቸው ኳሶች በጣም ቀላል ናቸው። በአቡበከር ሁለት ጎሎች ከዛም በወገኔ የተሳቱ ኳሶች ስታስበው ውጤቱን መቀየር ይቻል ነበር።”

ቡድኑ በአምስት ሳምንት ውስጥ ያረገው አጀማመር ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር…

“አንዳንዴ በደመነፍስ አንዳድንዴ በእውቀት የምትጫወተው አለ ፤ ማየት ያስፈልጋል። ቡድናችን አሁን ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ ነው። ቅርፅ እየያዘ ነው ብዬ ነው የማስበው። ያኔ በስሜት እና በፍላጎት ጥሩ ነበር ፤ ግን አሁን በዕውቀት። አሁንም የነበረብንን ችግር ማለት ያስተካከልናቸው ተጫዋቾች ወጥተውብናል። ከዛ ደግሞ ለማግኘት የነበረው ሂደት ብዙ አጥጋቢ አልነበረም። በተነፃፃሪ ዓምና የተሻለ ቡድን ነበረን። ነገር ግን አሁንም እሱን ለመስራት እየጣርን ነው ያለነው። አሁን ትንሽ ጊዜ ወስዶብናል ምክንያቱም ብዙ አዲስ ልጆች ስላሉ። ግን በሂደት እናስተካክለዋለን። ጥሩ ነው ፤ መምጣት የሚችል ነው።”

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለጨዋታው

“በጣም ጥሩ ጨዋታ ነው የተጫወትነው ፤ ሁለታችንም ጠንካራ ነበርን። መጫወት የምንፈልግበት የራሳችን የአጨዋወት ዘይቤ ነበር። በዛ አጨዋወት ዘይቤ ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ሰጥተው ጥሩ ውጤት ይዘን ወጥተናል።”

ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ስለቡድኑ ብቃት…

“አዎ ፤ ከዚህም በላይ የመስራት አቅም አላቸው። ሙሉ የተደራጀ ቡድን ነው ያለኝ። በማጥቃትም በመከላከልም ሚዛናዊ ቡድን ስለሆነ ያለኝ በአምስቱም ጨዋታ የተሻለ በማጥቃት መጫወት እንደምንችል አሳይተን ጥሩ ውጤት ይዘን ወጥተናል ብዬ አስባለሁ።”

ስለቡድናቸው ጠንካራ ጎን…

“እንደህብረት ማጥቃቱንም መከላከሉንም አብረው ይሰራሉ። ማድረግ ያለባቸውን እንቅስቃሴ አንዱ ቢበላሽበት አንዱ የተሰጣቸውን ሚና በአግባቡ ስለሚተገብሩ የተቀየሩትም የጀመሩትም የተሻለ ነገር ሰርተው ጥሩ ውጤት ይዘን ወጥተናል ብዬ ነው የማስበው።”

ዕረፍቱ ስለሚኖረው ተፅዕኖ…

“ከባድ ነው። ምክንያቱም ግለትህ ይወርዳል አጨዋወትህ እና የጨዋታ ብቁነትህ ወደ ጥሩ ነገር እየመጣ አንድ ወር ማረፍ ከባድ ነው። ያንን እንዴት እንደምናረግ አላውቅም። ለማንኛውም ቡድን ከባድ ነው ብዬ ነው የማስበው ፤ ወደ ጥሩ ግለት ከፍ ብለህ እንደገና ቀዝቅዘህ ነው የምትነሳው። ጨዋታዎችን አታገኝም ፣ የወዳጅነት ጨዋታም አይኖርም ፤ ሌሎቹ ሊጎች ስለሚጀምሩ ከባድ ነው ብዬ ነው የማስበው። ግን የተሻለ ነገር ለማድረግ እና ጠንካራ ጎናችንን አስቀጥለን ያሉብንን ድክመቶች ለማሻሻል እንሰራለን።”