የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ሹመት ነገ ይፋ ይደረጋል

ላለፉት ወራት ሲያነጋግር የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ቅጥር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱ ተጠቁሟል። በነገው ዕለትም ይፋዊ የፊርማ ሥነ ስርዓት ይደረጋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት ጥቂት ጊዜያት በቴክኒክ ዳይሪክተሩ ዳንኤል ገብረማሪያም መሪነት ጨዋታዎችን ሲያከናውን ቢቆይም ከፊቱ ከሚጠብቁት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በፊት አዲስ አሰልጣኝ እንደሚቀጥር ሲጠበቅ ቆይቷል። ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳስነበብነውም የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ለዚህ ኃላፊነት ከእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ጋር ንግግር ላይ ስለመሆናቸው ገልፀን ነበር።

ዛሬ ምሽት ይኸው የሁለቱ አካላት ንግግር ወደ ፍፃሜው መቃረቡን የሚያመለክት አስተያየት ከአሰልጣኝ ገብረመድህን መሰማቱ ደግሞ ከስምምነት መድረሳቸውን የሚያረጋግጥ ሆኗል። አሰልጣኝ ገብረመድህን ቡድናቸው በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈበት የምሽቱ ጨዋታ በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሹመታቸው አይቀሬ የመሆኑን ጉዳይ አስመልክቶ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

“በነገው ዕለት አንዳንድ ነገሮች ስምምነት ላይ እንደርሳለን ብለን እናስባለን ፤ ነገ ይፋ ይሆናል። ምንም የሚደበቅ ነገር የለም። ስለዚህ በነገው ዕለት መግለጫዎች ይሰጣሉ። እዛ ላይ ይፋ ይሆናል።”

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በማህበራዊ ትስስር ገፆቹ ምሽቱን ባጋራው መረጃ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ቅጥር ይፋዊ ስምምነት እና መግለጫ ነገ በፅህፈት ቤቱ እንደሚደረግ ይፋ አድርጓል።