መረጃዎች | 20ኛ የጨዋታ ቀን

ጠንካራ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብለው የሚጠበቁት ሁለት የአምስተኛው ሳምንት መገባደጃ የሆኑት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እነሆ !

ባህር ዳር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

ከሳምንቱ ጨዋታዎች መካከል ተጠባቂ የሆነው ፍልሚያ 09:00 ሲል ይጀምራል።

ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል በተቀሩት ሁለት ደግሞ የአቻ እና ሽንፈት ውጤቶች አስመዝግበው ሰባት ነጥቦች የሰበሰቡት ባህር ዳሮች ከሊጉ መሪዎች ላለመራቅ በሚያደርጉት ፍልምያ ውስጥ ሆነው ፋሲልን ይገጥማሉ። ውጤታማ ካደረጋቸው የባለፈው የውድድር ዓመት አጨዋወታቸው ሳይቀይሩ ጨዋታዎቻቸው በማካሄድ ላይ የሚገኙት የጣና ሞገዶቹ በሊጉ ከፍተኛው የግብ መጠን ካስመዘገቡ ክለቦች ተርታ ተቀምጠዋል። በየጨዋታው በአማካይ 2.2 ግቦች ያስቆጠረው ቡድኑ ከጊዮርጊስ ቀጥሎ ከፍተኛው የግብ መጠን ያስቆጠረ ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት ያለው የሊጉ ክለብ ነው። በዚህ ክብረ ወሰን ውስጥ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አጥቂው ሀብታሙ ታደሰም ከቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች በግምባር ቀደምነት ይጠቀሳል።

ቡድኑ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል አለው፤ በየጨዋታው እንደሚገጥመው ፈተና ቢሆን በርካታ ግቦች ባስተናገደ ነበር። አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በነገው ጨዋታ ይበልጥ የተጋለጠውና በአማካይ በጨዋታ 1.4 ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸውን ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ለተከላካይ ክፍሉ በቂ ሽፋን ያልሰጠው የአማካይ ክፍል ለውጦችን ይሻል። ባለፈው ጨዋታ አባይነህ ፊኖ ከገባ በኋላ የተጠቀሰው ችግር በመጠኑም ቢሆን ተቀርፎ እንደነበርም ይታወሳል።

በተከታታይ የአቻ ውጤት አስመዝግበው ቀዝቃዛ አጀማመር ያደረጉት ዐፄዎቹ በውጤት ረገድ ቀስ በቀስ ወደ ሚፈልጉት የድል መንገድ ተመልሰዋል።
ቡድኑ ሁለት የድልና ሁለት የአቻ ውጤቶች አስመዝግቦ ስምንት ነጥቦችም ሰብስቧል። ከነገው በወሳኝ ጨዋታ በፊት ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጣፋጭ ድል አስመዝግበው ወደ ተጠባቂው ጨዋታ ማምራታቸውም በሥነ-ልቦና ረገድ ያለው ጠቀሜታ ቀላል አይደለም። ፋሲል ከነማ አሁንም ጉልህ የአፈፃፀም ችግር የሚያይበት ቢሆንም በጊዜ ሂደት በርካታ መሻሻሎች ያሳየ ቡድን ነው። በተለይም በተከላካይ ክፍሉ ላይ የታየው መሻሻል በትልቁ ይነሳል።

ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ቢያስተናግድም ከዛ በኋላ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስተናግድ በመውጣት ትልቅ መሻሻል አሳይቷል። በነገው ጨዋታ ግን በጨዋታ በአማካይ 2.2 ጎሎች ያስቆጠረው ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ያለው ቡድን እንደመግጠማቸው ከወትሮ ለየት ባለ ጥንካሬ መግባት ይጠበቅባቸዋል። በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ተጋጣምያቸው ከኋላ የሚተወው ሰፊ ክፍተት ዒላማ ያደረገ የማጥቃት አጨዋወት የነበራቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በነገው ዕለትም በማጥቃቱ ላይ የጎላ ድርሻ ያላቸውን የባህር ዳር የመስመር ተከላካዮች ዒላማ ማድረጋቸው አይቀሪ ነው።

ከወሳኙ ጨዋታ አስቀድሞ ባህር ዳሮች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በተቃራኒው ባለፈው ጨዋታ ያልተሳተፉት ቸርነት ጉግሳ እና ፍሬው ሰለሞን ከጉዳት ተመልሰዋል። ፋሲሎችም በተመሳሳይ ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነው ስብስባቸውን ይዘው ወደ ተጠባቂው ጨዋታ ያመራሉ።

ፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ በሊጉ 8 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል ሁለት ጊዜ አሸንፎ አምስት ጨዋታዎችን አቻ ሲለያዩ ባህር ዳር ከተማ ዓምና የመጀመሪያው የእርስ በርስ ድሉን በ2-1 ውጤት አስመዝግቧል። በጨዋታዎቹ ፋሲል ስምንት ጎሎችን ባህር ዳር ደግሞ አራት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ የዓመቱ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ይመራል። ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ ረዳቶች ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በበኩሉ አራተኛ ዳኛ በመሆን ለጨዋታው ተመድበዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

በአንድ ነጥብ ብቻ ተበላልጠው የሚገኙትን ሁለት ክለቦች የሚያገናኘው እና ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቀው ጨዋታ አምስተኛውን ሳምንት ይቋጫል።

ባለፈው ሳምንት የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ያስተናገዱት ቡናማዎቹ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ከጦና ንቦች ጋር ይፋጠጣሉ። በውድድር ዓመቱ ከኳስ ውጭ ከፍ ባለ ጫና ውስጥ የሚጫወት እና በመስመሮች ለማጥቃት የሚሞክር ቡድን የገነቡት አሰልጣኝ ኒኮላ ካቫዞቪች ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ በአብዛኛው ቀጥተኛ አጨዋወት ምርጫቸው አድርገዋል ፤ ሆኖም በአጨዋወቱ በርካታ ግቦች ማስቆጠር አልቻሉም። በአራት ጨዋታዎችም አራት ግቦችን አስቆጥረዋል። ይህም ዝቅጠኛ ግቦች ካስቆጠሩ የሊጉ ክለቦች ያደርጋቸዋል።

አሰልጣኙ ባለፉት ጨዋታዎች የተለያየ የአጥቂ ጥምረቶች መጠቀማቸውና ከፋሲሉ ጨዋታ በኋላ በሰጡት አስተያየት መሰረት በነገው ጨዋታ ጥምረቱ ላይ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የነገው ተጋጣምያቸው በአራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ባለቤት መሆኑም ግብ የማስቆጠር ፈተናው ከባድ ያደርግባቸዋል። አሰልጣኙ ከዚህ በተጨማሪ በመጀመርያዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ ከቆየ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አራት ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸው ወደ ቀድሞ ጥንካሬው የመመለስ ኃላፊነት አለባቸው።

ከአራት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል አድርገው ሁለት ጨዋታዎች ላይም ሽንፈት የገጠማቸው ወላይታ ድቻዎች ምንም እንኳ ጥሩ የኳስ ፍሰት ያለውና ወጥነት የሚታይበት የጨዋታ መንገድ ቢኖራቸውም በውጤት ረገድ ግን ወጥነት ይጎድላቸዋል። በአራቱም ሳምንታት በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ማግኘት ተስኗቸዋል። በነገው ጨዋታም ከሽንፈት መልስ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደመሆኑ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ላለመጣል ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ኳስን ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚሞክርና ጠጣር የተከላካይ ክፍል ያለው ቡድን ገንብተዋል። በአራት ጨዋታዎች የተቆጠረባቸው የግብ መጠንም ሁለት ብቻ ነው። ይህ ቁጥርም የሊጉ ዝቅተኛ ግብ ያስተናገደ ክለብ ያደርጋቸዋል። ሆኖም በአጥቂ ክፍላቸው ላይ የሚታየው ዕድሎች ያለመጠቀም ትልቅ ችግር ቡድኑ አንድ እርምጃ እንዳይሻገር አድርጎታል። ቡድኑ የግብ ዕድሎች የሚፈጥሩ አማካዮች ቢኖሩትም የአፈፃፀም ችግሩ ግን የጎላ ነው። ቡድኑ በአማካይ በጨዋታ 0.5 ግብ ብቻ የማስቆጠሩ ምክንያትም ይህ ከፍተኛ የአፈፃፀም ችግሩ ነው። አሰልጣኙም ይህንን በተደጋጋሚ ጊዜ በቡድኑ ላይ የሚታየውን ችግር የመቅረፍ የቤት ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

የቡድን ዜናዎችን ስንመለከት በወላይታ ድቻ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ከሜዳ ከራቀው ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ በቀር የተሰማ አዲስ የጉዳት ዜና የለም። በኢትዮጵያ ቡና በኩልም በተመሳሳይ የረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው አማካዩ ሮቤል ተክለሚካኤል ውጪ ቀሪው ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ ነው።

በ18 ጊዜ የክለቦቹ የቀደመ ግንኙነት 9 የአቻ ውጤቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዘዋል። በቀሪዎቹ ፍልሚያዎች ወላይታ ድቻ አምስቱን ሲረታ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አራቱን አሸንፏል። በእነዚህ 18 ጨዋታዎች አጠቃላይ 26 ጎሎች ሲቆጠሩ ቡድኖቹ እኩል 13 13 ግብ በስማቸው አስመዝግበዋል።

ጨዋታውን ኤፍሬም ደበሌ በዋና ዳኝነት ሲዳኘው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና አሸብር ታፈሰ በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይመዋል።