እሳቶቹ ትውልደ ኢትዮጵያዊውን ሸልመዋል

በአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር ተሳታፊ የሆነው ቺካጎ ፋየር ማረን ኃይለስላሴን ሸልሟል።

በአሜሪካ ሜጀር ሊግ ሶከር የሚሳተፈው ቺካጎ ፋየር የውድድር ዓመቱ መጠናቀቁን ተከትሎ የክለቡ ኮከቦችን ይፋ ሲያደርግ በውድድር ዓመቱ ስድስት ግቦች አስቆጠሮ የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ለሆነው ለትውልደ ኢትዮጵያዊው ማረን ኃይለስላሴ የወርቅ ኳስ ሸልሟል።

የእሳቶቹም ማልያ ለብሶ በተጫወተባቸው 32 ጨዋታዎች ስድስት ግቦች በማስቆጠር ሦስት ግብ የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ያቀበለው ይህ የመስመር ተጫዋች በሦስት ጨዋታዎች ቡድኑን ተሸክሞ ወጥቷል። ሁለት ግቦች ባስቆጠረበት ከኢንተር ማያሚ ጋር በተደረገው ጨዋታ፤ አንድ ግብ እና አንድ ለግብ የሆነ ኳስ ያቀበለባቸው የአታላንታው እና የሞንትርያሉ ጨዋታ ተጫዋቹ ብቃቱን ያሳየባቸው ነበሩ።

ከስዊዘርላንዱ ሉጋኖ ወደ አሜሪካው ክለብ በውሰት ሲጫወት የቆየው የ24 ዓመቱ ተጫዋች የውሰት ውሉ በዲሰምበር 31 ካበቃ በኋላ ቀጣይ ማረፍያው ይታወቃል። ታናሽ ወንድሙ ቅዱስ ኃይለስላሴም በስዊዘርላንዱ Fc wil 1900 እየተጫወተ ይገኛል።