በድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም የአርቴፊሻል ሳር ተከላን አስመልክቶ የከተማዋ ከንቲባ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል

👉   “ተጫዋቾች እዚህ ሜዳ መጥተው ሲጫወቱ ሜዳውን ይወዱታል”

👉  “ይህን በሙሉ ልብ ነው የምናገረው ፤ ብሔራዊ ቡድናችን በሜዳ ችግር ሊከራተትም አይገባም”

👉  “ድሬዳዋ ላይ ቃል ቃል ነው! የተባለ ነገር ይፈጸማል”


👉 “አንዱ በር በጆቫኒ ባርባኖ እንዲሆን ተወስኗል። የተረጋገጠ ለምርጫ የማይቀርብ ነገር ነው”

ድሬዳዋ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ወቅቱ በሚጠይቀው ደረጃ የመጫወቻ ሜዳውንም ሆነ ሌላውን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በማሰብ በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ክቡር ከድር ጁሀር ትዕዛዝ የገንዘብ ድጋፍ እና የቅርብ ክትትል ደረጃውን የጠበቀ የፊፋን መስፈርት ያሟላ ዘመናዊ አርቲፊሻል ሳር የማንጠፍ ሥራ ተጀምሮ ወደ መጠናቀቁ ደርሷል። ዛሬም የተለያዩ የከተማው አመራሮች በተገኙበት የአርቴፊሻል ሳር ተከላው ያለበትን ሂደት የምልከታ ጉብኝት በተደረገበት ወቅት በስፍራው ለተገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሀር ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ እንዲህ አቅርበነዋል።

ክቡር ከንቲባ ኳስ በጣም እንደሚወድ ሰው በኳስ ውስጥ በየሳምንቱ እንደሚያሳልፍ ሰው የድሬዳዋ ስታዲየም በሜዳ ችግር ምክንያት ውድድር አላደረገም ሲባል ይህን ስታስብ በውስጥህ ምንድን ነበር የምታስበው ?

አንደኛ እውነት ለመናገር ይሄንን ሜዳ በፊትም እኔ ራሴ ነኝ የጀመርኩት። ሜዳ ከመጀመሩ አኳያ ውጪም ሙሉ ለሙሉ አሁን የውስጥ የስፖርት መንፈስም ስላለኝ በዛ መልኩ ያለው ነገር ላይ ለማስቀጠል እና ለማሳደግ የተሻለ ነገር እንሠራለን ብለን አቅደን ነው እየሠራን ያለነው ፤ ያንንም በምንፈልገው ልክ ነው እየሠራን የምንገኘው።

10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ያስተናገደ ስታዲየም ነው በዚህ ደረጃ የሜዳ ዕድሳት ተደርጎለት አያውቅም አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ብቸኛው የፊፋን ፍቃድ ያሟላ ሠው ሠራሽ ሜዳ ሊሆን ነው። ዛሬ ላይ ሆነህ ያንን ስታስበው እንዴት ነው የምታነጻጽረው?

እኔ ያኔ 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ሲያዘጋጁ የነበረው ምን ያህል ብሩህ ተስፋ እንዳላቸው ነገ እኛ ባናሻሽልም ትውልዱ በሚመጥነው መልኩ ያሻሽለዋል ብለው የሠሩትም ስለሆነ እኔ በዚሁ አጋጣሚ አብዛኞቹ ስለሌሉ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በገነት ያኑረው። አሁን የእነሱን ኃላፊነት አደራ ተቀብለን ድሬዳዋን በዚህ መልኩ እንዲያምርባት የሕዝብ አገልጋይ እንደመሆናችን መጠን ሌት ተቀን ነው በምንችለው አቅም እየሠራን የምንገኘው እና ለእኔ ትልቅ ዕድል ነው ፤ በእኔ ጊዜ መሠራቱ በዚህ ዘመን መሠራቱ በተለይ በብልጽግና ዘመን ፤ በጣም ደስ ይለናል እና ይሄን እናስቀጥላለን ብዬ ነው የማስበው።

በኢትዮጵያ ሁልጊዜ እንደሚባለው ስታዲየሞች ይጀመራሉ እንጂ አያልቁም በፌስቡክ ገጽህ ላይ “ቃልኪዳናችንን ጠብቀን ሪቫኑን እንደምንቆርጥ…” የሚል ቃል አስፍረሃልና ምን ትምህርት ይሰጣል?

ትዝ የሚላችሁ ከሆነ ባለፈው ዓመት በድሬዳዋ ስታዲየም እንደዛ ሲወረደብን ምን ብለን እንደነበረ ትዝ ይላቹኋል ። እኛ ወቅታችንን ጨርሰናል። ፌዴሬሽኑ ስለለመነን ለአንድ ወር ወይም ለ14 ሳምንት ጨዋታ አራዝሙልን ስላሉ የእነርሱን ተቀብለን ነው። በወቅቱ የፈጣሪ ጉዳይ ነው ዝናብ ዘንቧል። ስንተችም ስለነበረ የሚቀጥለው ዓመት እንለመናለን ብያለሁ። አሁንም ቢሆን ተለምነን ነው ሜዳው ላይ ጨዋታ የሚደረገው ። በእኛ ፕሮግራም እንጂ በሰው አንመራም ቢሆንም በተሻለ መልኩ ይህን ሂደታችንን እናስቀጥላለለን ብዬ የማስበው። ፕሮፌሽናል የሆነ ተጫዋቾች እዚህ ሜዳ መጥቶ  ሲጫወት ሜዳውን ይወደዋል። ሌላ ሀገር ላይ አይታቹሁ ከሆነ አርቴፊሸል ሳር ላይ ሲሚንቶ ይደረጋል። ሳሩን አምጥቶ ከላይ ይነጠፋል። ይሄ ጉልበት እና ቁርጭምጭሚት ላይ ለተጫዋች ጉዳት ነው የሚያመጣው እና በለፋህበት ልክ ስለማይመጣ ጉዳቱ ያመዝናል። የእኛ ግን ረበር አለው ከስር በተለይ ለተጫዋች የሚመች ነው። አፈር ላይ እንደምትጫወት ነው ምቾቱ በኋላ ላይ ማየት ይቻላል። ቃላችን እና ሪቫናችን ያልንበት ምክንያት እኛ የማንፈጽመውን ነገር አንናገርም። ይህ ነው ድሬዳዋ ላይ ቃል ቃል ነው! ያለውን ነገር ይፈጽማል። ለሚዲያ ለመታየት ሳይሆን በተግባር ቆርጠን እንጨርሳለን ብዬ አስባለሁ።

መግቢያ በሮቹን በታዋቂ ሰዎች ለማድረግ ስለመታሰቡ ?

እርሱን ጨርሰናል አሁን ግን የስፖርት ቤተሰቦች ጋር እንወያያለን በማን ስም ይሁን አምስት በሮች አሉ ፤ ያዘጋጀናቸው ስሞች አሉ ግን  ደግሞ የስፖርት ቤተሰቡም እናወያያለን። የጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ፣ ተከበ ዘውዴ ወይም በሌሎቹ ይሁን የሚለው ይወሰናል። ግን አንዱ በር በጆቫኒ ባርባኖ እንዲሆን ተወስኗል። የተረጋገጠ ለምርጫ የማይቀርብ ነገር ነው። ጆቫኒ በህይወት እያለ የሰራው አስተዋፆኦ ስለሆነ ውለታ አንረሳም። ቢያንስ ዋናዋን ቪአይፒ መግቢያዋን  በእርሱ ስም ለማድረግ አስበናል። ድሮ የሚታወቀው ባቡር በር እና ኮተን በር ነበር የሚታወቀው አሁን በዛ መልክ ይህን ስያሜ እንሰጣለን ብዬ አስባለሁ።

የመጨረሻ የዋልያዎቹ ጨዋታ ከጅቡቲ ጋር እዚህ ነው የተጫወተው ከዛ በኋላ ከሀገር ውጭ ነው እየተጫወተ የሚገኘው ይህ ጨዋታ እዚህ በመደረጉ በግልህ የፈጠረልህ ስሜት ካለ ?

ለሀገሪቷ ምን አስተዋፅዖ አደረግኩ እንጂ ሀገሪቷ ለኔ ምን አስተዋፅዖ አደረገች የሚል አስተሳሰብ የለኝም። ያኔ የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት እንደሚታወቀው የድሬደዋ ህዝብ ጥሩ ለተጫወተ ነው የሚደገፈው በወቅቱ የፌዴሬሽን ሰዎች ተቀይመውን ነበር ጥሩ ለተጫወተው ጂቡቲ ህዝቡ ተገልብጦ ሲደግፍ ምንድነው ድሬደዋ ለጎረቤት ነው የሚያደሉት ይባል ነበር። አሁንም ቢሆን የድሬደዋ ህዝብ ነፃ ፣ ገለልተኛ ነው የእግርኳስ ፍቅር አለው። በመጀመርያ ግን ለሀገር ቅድሚያ የሚሰጥ ነው።  ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ ትኩረት ካደረጉባቸው ጉዳዮች አንዱ የሜዳ ነበር። ሜዳ ስትሠሩ ጥራት ይኑረው፤ ለዚ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀትም ወሳኙ ነገር የሜዳ ጥራት ጉዳት ነው ብለውን ነበር። እኛም እሱን ተከትለን የደህንነት ካሜራ፣ Vip ክፍሎች፣ ሊፍትና ሌሎች ያሟላ ስቴድየም እየሰረን ነው። ይሄን እውን እናደርጋለን፤ ይህን በሙሉ ልብ ነው የምናገረው ብሄራዊ ቡድናችን በሜዳ ችግር ሊከራተትም አይገባም። የብሔራዊ ቡድኑ ውድድሮች ወደዚህ የሚመጡበት ነገር እሩቅ አይሆንም።