የኢትዮጵያ ዋንጫ | የመክፈቻ ቀን ውሎ

የ2016  የኢትዮጵያ ዋንጫ ዛሬ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እና በሐዋሳ ሠው ሠራሽ ሜዳ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ጅማሮውን አድርጓል።

በጫላ አቤ

ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ተብሎ ይጠራ የነበረው ውድድር ዘንድሮ የኢትዮጵያ ዋንጫ በሚል ስያሜ የተመለሰ ሲሆን ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 24 ውድድሩ በይፋ ተጀምሯል። በመክፈቻው ቀንም አራት ጨዋታዎች በሁለቱም ስታዲየሞች ተደርገዋል።

*በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የተደረጉ ጨዋታዎች

ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ 2-0 ጅማ አባ ቡና

8 ሰዓት ላይ የተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ እና ጅማ አባቡናን ያገናኘ ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ተደርጎበታል። በጅማ አባቡና በኩል ጥሩ የሚባል የጨዋታ ፍሰት እና የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ሲያስመለክተን በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በኩል ፈጣን በሆነ መልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎም 25ኛው ደቂቃ ላይ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በመልሶ ማጥቃት በይትባረክ በክሪ አማካኝነት ግብ አስቆጥሮ በመምራት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ቀጥሎ 82ኛው ደቂቃ ላይ የጅማ አባቡናው ሱራፌል ገዙ ራሱ ላይ ግብ በማስቆጠሩ ኦሮሚያ ፖሊስ በ 2-0 ድል ወደ ሁለተኛው ዙር ተሸጋግሯል።

– በተመሳሳይ ሰዓት በሀዋሳ ሠው ሠራሽ ሜዳ በተደረገው ጨዋታ ነገሌ አርሲ በያሬድ ተስፋዬ ብቸኛ ግብ ቦዲቲ ከነማን 1-0 ረቷል።

ንብ 1-4 ሀላባ ከተማ

10፡00 ሲል በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የተደረገ ሲሆን በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ንቦች ጥሩ የግብ እድል ፈጥረው መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታው በዚህ ሂደት ቀጥሎ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ 45ኛ ደቂቃ ላይ የሀላባ ከተማ ተጫዋች የሆነው ከማል አቶም የመታውን ኳስ አሌክስ ተሰማ በራሱ ላይ በማስቆጠር ሀላባ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። አጋማሹም በዚሁ ውጤት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በአመዛኙ የሀላባ ከተማ የበላይነት የታየበት አጋማሽ ሲሆን በ50ኛው ደቂቃ ሀላባ ከተማዎች ያገኙትን የቅጣት ምት ፀጋ ክፍሌ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮት የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት አሳድጓል። ሆኖም ንቦች ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በድጋሚ ሀላባ ከተማዎች በ59ኛው ደቂቃ ያገኙትን የግብ ዕድል ከማል አቶም ከርቀት አስቆጥሮት የግብ ልዩነቱን ማስፋት ችሏል። ሆኖም ንቦች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ 70ኛው ደቂቃ ላይ በሀላባ ከተማ ተከላካይ ስህተት የተገኘውን ኳስ ናትናኤል ሰለሞን ያስቆጠረ ሲሆን ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ 83ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ በቀለ ለሀላባ ከተማ አራተኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም በሀላባ ከተማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ሀላባ ከተማ ወደ ሁለተኛው ዙር አልፏል።

– በተመሳሳይ ሰዓት በሀዋሳ ሠው ሠራሽ ሜዳ በተደረገው ጨዋታ ካፋ ቡና አሶሳ ከተማን 3ለ0 ረቷል። በዚህም ካፋ ቡና በዕለቱ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈ አራተኛው ክለብ ሆኗል።